ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የአፍሪካ የስራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የአፍሪካ የስራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም እንደምታስተናግድ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በሰጡት መግለጫ ፎረሙ አፍሪካ ያላትን ወጣት የሰው ሃይል ለልማት በመጠቀም የአፍሪካን ልማትና ህዳሴ ማሳለጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የሚመክር ነው።

የአፍሪካ አገራት በስራ እድል ፈጠራ በተናጠል የሚያከናውኑት ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ በትብብር እድሎችን ለመጠቀምና ተግዳሮቶችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚካሄድ መሆኑንም ጨምረዋል። 

በአህጉሪቱ የአለም ተለዋዋጭ ሁኔታንና የስራ ገበያን ታሳቢ ያደረገ ወጣት የሰው ሃይል ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑን በመግለጽ ፎረሙ ልምዶችን በመለዋወጥ ፖሊሲ ለማመንጨትና ለመተግበር  አጋዥ ነው ብለዋል።

ሶስተኛውን የአፍሪካ የስራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ግብርናን በማዘመን የስራ ዕድል መፍጠር፣ የፋይናንስና ዲጂታል አካታችነት  ትኩረት የሚያደረግባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአህጉሪቱ በስራ እድል ፈጠራ የተያዙ እቅዶች ላይ በመምከርና የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚመላከቱበት ገልጸዋል። 

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ በአፍሪካ የሚገኙ አስቻይ ሁኔታዎችን በመጠቀም ገበያና የስራ እድልን በትብብር ለመፍጠር ምክክር ይደረጋል ብለዋል።

ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ቀደም ሲል የተካሄዱ ሁለት የስራ እድል ፈጠራ ፎረሞች በአፍሪካ የኤሌክትሮኒክስ ስርአትን በመዘርጋት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን በስራ እድል ፈጠራ፣ በገበያ መረጃ ስርአት፣ በዲጂታል መታወቂያና በሌሎች ዘርፎች በስራ እድል ፈጠራ ያከናወነቻቸውን ተግባራት በፎረሙ ታቀርባለች ብለዋል።

ኢንቨስተሮች ፣ተመራማሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ኢንተርፕራይዞችና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች በጉባዔው የሚሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና ከአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ ግሩፕ ጋር በመተባበር ፎረሙን ማዘጋጀቷ በመግለጫው ተጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም