የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጡ የአሰራር ማዕቀፎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጡ የአሰራር ማዕቀፎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው
አዳማ፤ሰኔ 27/2017 (ኢዜአ)፦የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጡ የአሰራር ማዕቀፎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።
8ኛው ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ፎረም እና የአካል ጉዳተኞች የምርጫ ተሳትፎ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በሥራ ስምሪት፣በትምህርት፣በጤና እና በፍትህ ተደራሽነት እና ሌሎችም ዘርፎች አካል ጉዳተኞች በብዛት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።
ለዚሁ ማስፈፀሚያ የወጡ አዋጆችና መመሪያዎች ተግባራዊ በመደረጋቸው ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ይገኛልም ነው ያሉት።
በመሆኑም የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጡ የአሰራር ማዕቀፎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል።
የመድረኩ ዓላማም የአካል ጉዳተኞችን የምርጫ ተሳትፎ ለማጠናከር የባለ ድርሻ አካላት እገዛና ተሳትፎ እንዲጎለብት መሆኑን አንስተው፥ በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ የአካል ጉዳተኞችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ፎረም ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጠናከርና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉም እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሥርዐተ ፆታ እኩልነት እና ማህበራዊ አካታችነት የሥራ ክፍል ተወካይ ወይዘሮ ዮርዳኖስ ተወልደ፤ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሀዊ፣ አካታች፣ ነጻ፣ አሳታፊ እና ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲካሄድ የህብረተሰብ ውክልናን ማረጋገጥ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የአካል ጉዳተኞች የምርጫና የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጠናከር የህግ ማእቀፍ ጭምር መውጣቱን አስታውሰው፥ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካል ጉዳተኞች የነበራቸውን ተሳትፎና ውክልና በማጥናት ለቀጣይ ምርጫ የተሻለ ውክልና እንዲኖራችው እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የዛሬው መድረክም ዋነኛ ዓላማ ከዚሁ ጋር የተገናኘ መሆኑን ጠቁመው፥ በእውቀት እና በጥናት ላይ ተመስርቶ የአካል ጉዳተኞችን የምርጫ ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት፣መንግሥታዊ ያልሆኑ እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።