የኢትዮጵያ ስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
በ2017 በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትላንት ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ የውጭ ሀገር ስምሪትና በርቀት ስራ የተጀመሩ ስራዎች ዘመናዊ በሆነ መንገድ መከናወናቸው የሚበረታታ መሆኑን መግለጻቸው ይታወቃል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የ2017 በጀት አመት አፈጻጸምን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ የተተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ብዙ ዕድል ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ከዝግጅት አንስቶ ሰፊ ስራ መሰራቱንና ከልማት አቅጣጫዎች ጋር ተሰናስሎ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው፤ በክህሎት የሚመራ የስራ ዕድል ተግባራዊ መደረጉ ለዘርፉ አፈጻጸም ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
የዘርፉ አፈጻጸም በየዓመቱ በአማካይ ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል እየተፈጠረ መምጣቱን አስታውስዋል።
በተለይም በ2017 በጀት ዓመት ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸው፤ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ማድረጋቸውን አመላክተዋል።
ለዚህም ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ ከ180 በላይ አዳዲስ ስርዓተ ትምህርቶች መቀረጻቸውን ተናግረዋል።
የግሉ ዘርፍ በስራ ዕድል ፈጠራው ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንና የኢንተርፕራይዞች የመክሰም ምጣኔም መቀነሱን አመላክተዋል።
በጊዜያዊነት የሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች በሪፖርት እንደማይካተቱ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለስራ ዕድል ፈጠራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
አሁንም ስራ ፈላጊዎች በዚህ ስርዓት እንዲመዘገቡ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘርፉ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያ የሆኑ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን አመልክተው፤ አዳዲስ የስራ መዳረሻዎችን ወደ አውሮፓ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዜጎች በህጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲያደርጉ በማበረታታት የሚያጋጥማቸውን ችግር መፍታት መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ጊዜያትም የተገኙ ውጤቶችን የሚያስቀጥሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት የመንግስት አፈጻጸምን ባቀረቡበት ወቅት በዓመቱ ለ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንና ዘርፉ ትልቅ እመርታ የታየበት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።