በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞችን በሳይንሳዊ መንገድ በመትከል እንዲጸድቁ ማድረግ ያስፈልጋል - የግብርና ሙያተኞች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞችን በሳይንሳዊ መንገድ በመትከል እንዲጸድቁ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ የግብርና ሙያተኞች አስገነዘቡ። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በዜጎች የነቃ ተሳትፎ ያለፉት ሰባት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሀገርን የደን ሽፋን በማሳደግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በማበርከት ላይ ይገኛል።

የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም "በመትከል ማንሰራራት'' በሚል መሪ ሃሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ግብን አስጀምረዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለማሳደግ ሊደረጉ የሚገባቸውን የተከላ ጥንቃቄ ሥርዓት በሚመለከት የዘርፉን ሙያተኞች አነጋግሯል።

በግብርና ሚኒስቴር የሥነ-ሕይወታዊ የአፈርና ውሀ ጥበቃና ጥምር ደን እርሻ ዴስክ ኃላፊ በፍቃዱ ብርሃኔ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በተያዘው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ኢትዮጵያዊያን ችግኞችን በሳይንሳዊ መንገድ በጥንቃቄ በመትከል ለታለመላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማ ማዋል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት የልማት አጀንዳ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በተከላ ወቅትም ላስቲኮችን አንስቶ መትከልና የተቆፈረውን አፈር በአግባቡ ወደ ቦታው መመለስ ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር ስንታየሁ መንግስቱ እንደገለጹት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚሳተፉ ዜጎች ችግኞችን በጥንቃቄ መትከል ይኖርባቸዋል።

በመርሃ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ማሻሻል በሚያስችል መንገድ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ አሻራቸውን ማሳረፍ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተፋሰስ ልማት ስራ የተዘጋጁ ጉድጓዶች ያቆሩትን ውሃ በማፋሰስ ለሚተከሉ ችግኞች ጽድቀት  በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሥነ-ሕይወታዊ የአፈርና ውሀ ጥበቃና ጥምር ደን እርሻ ዴስክ ኃላፊ በፍቃዱ ብርሃኔ÷ ዜጎች በችግኝ ተከላ የሚያደርጉትን የነቃ ተሳትፎ ተንከባክቦ በማጽደቅ መድገም ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬታማ ለማድረግ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተሰርቷል ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር ስንታየሁ መንግስቱ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም