ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ጉባዔን ለማካሄድ የሚመራበትን ስርዓት ጨምሮ የዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ነው- ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔን ለማካሄድ የሚመራበትን ስርዓት ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊዎች ልየታ መጠናቀቁን የጠቀሰው ኮሚሽኑ በትግራይ ክልልም በቅርቡ ለማካሄድ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብሏል።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በሰጡት መግለጫ የአጀንዳ ቀረጻ ለማካሄድም የአሰራር ሥርዓት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በየፈርጁ እየተደራጁ ነው ብለዋል።

ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ጉባዔው የሚመራበት የአሰራር ሥርዓት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ለዚህም የኮሚሽኑን አማካሪ ኮሚቴ ጨምሮ በየደረጃው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ግብዓት እንዲሰጡ እየተደረገ  መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ለምክክር ጉባኤው አመቻቾችና አወያዮችን ለመምረጥ መስፈርቶች ተዘጋጅተው የመለየት ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በትግራይ ክልልም የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክሩን ተሳታፊዎች ልየታ ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራን እና በአዲስ አበባ ነዋሪ  ከሆኑ የክልሉ ተወላጆች ጋር ውይይት ማድረጉን አክለዋል።

የዳያስፖራ ማህበረሰብም በምክክሩ እንዲሳተፍ ዝግጅቶች መጀመራቸውን አንስተዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባራት አሁንም መቀጠላቸውን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት በቅርቡ የምክክር አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ወሳኝ የሆነው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ትግራይ ክልልን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካል በሂደቱ በመሳተፍ በጎ ሚና እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወቅ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም