ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ አማራጮችን በመጠቀም ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅ ረገድ የድርሻችንን እንወጣለን - መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ አማራጮችን በመጠቀም ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅ ረገድ የድርሻችንን እንወጣለን - መምህራን
ሚዛን አማን፣ ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ አማራጮችን በመጠቀም ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅ ረገድ በሚከናወኑ ተግባራት የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለጹ።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እንደገለጹት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ፖሊሲ የሀገር ሕልውናን አስጠብቆ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ መሠረት ያደረገ ነው።
በመሆኑም ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ አማራጮችን በመጠቀም ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስከበሩ ረገድ በሙያችን የሚጠበቅብንን ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
በዩኒቨርስቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ቢመርቅ በሪሁን ዓለም አቀፍ የወደብ አጠቃቀም ሥርዓቶችን ተከትሎ የባሕር በር ጥያቄ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ለዚህም በሙያቸው ጥናትና ምርምሮችን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አክለዋል።
የጎረቤት ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት በሚያስቀድመው የዲፕሎማሲ ፖሊሲ፥ ሰላማዊና አፋጣኝ ምላሽ የሚገኝበት አካሄድ ላይ ግልፅ ሊሆኑ የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉ በተጨማሪ መረጃዎች በማደራጀት ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚተጉም አመልክተዋል።
ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ አዎንታዊ ተጽዕኖ የፈጠረውን የዲፕሎማሲ አቅምን በማጉላት በባህር በር ጉዳይ ላይም መድገም እንደሚጠበቅ ነው መምህር ቢመርቅ በአፅንኦት የገለጹት።
ለዚህ ደግሞ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ አማራጮችን መከተልና ዜጎች በሚያገኙት አማራጮች ለጉዳዩ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ በማድረግ ረገድ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
ታሪካዊ ዳራን ተንተርሶና እውነትን በመከተል ለኢትዮጵያ ልዕልና የባሕር በር ማግኘት ጉዳይን ማሳካት ግድ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አለማየሁ አብርሃም ናቸው።
በእውቀት እየተመራ ያለው ሀገራዊ የዲፕሎማሲ ሥራ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ማስጠበቅ እየቻለ ነው ብለዋል።
በሰጥቶ መቀበል መርህ የተፈጥሮ ሀብትን በጋራ የመጠቀምና በጋራ የማደግ ዓላማ ያለው ሰላማዊ የባሕር በር ጥያቄ ከትናንት ታሪክና ጂኦግራፊያዊ ቅርበት አንጻር ማሳካት እንደሚቻልም አረጋግጠዋል።
ጉዳዩ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅ በመሆኑ ያለምንም የፖለቲካ፣ የብሔርና መሰል ልዩነቶች እንደ ዓድዋና የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በአንድነት መቆም የሚያስፈልገው መሆኑንም ምሁራኑ አንስተዋል።