የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪያ ከተሞች የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ ወደ 31 ከፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪያ ከተሞች የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ ወደ 31 ከፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪያ ከተሞች የሚያደርገውን ሳምንታዊ የመንገደኞች በረራ ወደ 31 ከፍ ማድረጉን አስታውቋል።
ናይጄሪያ የአየር መንገዱ የአፍሪካ ትልቋ መዳረሻ ሀገር እንደሆነችም ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም ወደ ናይጄሪያ ሌጎስ የሚያደርገውን ዕለታዊ በረራ ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ በአገልግሎት ዘርፉ ከተመዘገቡ እድገቶችና ውጤቶች መካከል አንዱ ማሳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በተያዘው ዓመት ተጨማሪ 13 አውሮፕላኖችን በመግዛት አጠቃላይ የአውሮፕላን ብዛቱ 180 መድረሱን መጠቆማቸውም ይታወሳል።
ስድስት ተጨማሪ አዳዲስ መዳረሻዎችን በመጨመር አጠቃላይ ያለውን የመዳረሻ ብዛት ወደ 136 ማሳደጉንና በተያዘው ዓመት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ከ19 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ማጓጓዙንና ይህ ከለውጡ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ገደማ መጨመሩን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ወደ ንግድ ከተማዋ ሌጎስ የጀመረውን ተጨማሪ ዕለታዊ በረራ አስመልክቶ የተዘጋጀ መርሃ ግብርም ተከናውኗል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የናይጄሪያ የአቪዬሽን እና ኤሮስፔስ ሚኒስቴር መሪ ስራ አስፈጻሚ ኢብራሂም ካና(ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ሲቪል አቪዬሽን ተወካዮች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የጉዞ ወኪሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የናይጄሪያ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ ፍሬህይወት መኮንን አየር መንገዱ አቡጃ፣ ሌጎስ፣ ካኖ እና ኢኑጉ ከተሞች የመንገደኛ በረራዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በአቡጃ፣ ሌጎስ እና ካኖ ከተሞች ሳምንቱን ሙሉ እንዲሁም በኢኑጉ በሳምንት ሶስት ጊዜ አየር መንገዱ እንደሚበር አመልክተዋል።
በሌጎስ የሚያደርገውን ዕለታዊ በረራ ወደ ሁለት በማሳደግ በከተማዋ ያለውን ሳምንታዊ የበረራ ቁጥር ወደ 14 ከፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ይህም አየር መንገዱ ወደ ናይጄሪያ ከተሞች በሳምንት የሚያደርገውን የመንገደኞች በረራ ቁጥር ወደ 31 ከፍ አድርጎታል ነው ያሉት ስራ አስኪያጇ።
ወደ ሌጎስ የሚደረገው በረራ መንገደኞች በፈለጉት ሰዓት በረራቸውን ማድረግ የሚችሉበትንና ናይጄሪያም የትራንስፖርት ትስስሯን እንድታሳድግ የሚያስችል ተጨማሪ አማራጭ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ናይጄሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ትልቁ መዳረሻ ናት ያሉት ስራ አስኪያጇ በመንገደኞች ብዛት፣ በበረራ ቁጥር ትልቅ የገበያ አቅም እንደሆነች ተናግረዋል።
ከመንገደኞች በረራ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪያ በሳምንት ከ30 በላይ የካርጎ በረራ እንዳለውም ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በአቪዬሽን ዘርፍ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው አየር መንገዱ እ.አ.አ ኖቬምበር 1960 በረራ መጀመሩንና ይህም ናይጄሪያ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች አንድ ወር በኋላ መሆኑ ታሪካዊ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ወደ ናይጄሪያ ሳይቋረጥ በረራዎችን ማድረጉንና በየጊዜው የሚያጓጉዛቸውን መንገደኞችና የበረራ ቁጥር እያሳደገ መምጣቱን ነው ያብራሩት።
አየር መንገዱ ለናይጄሪያ የአቪዬሽን ዘርፍ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች በየሀገራቱ በርካታ መዳረሻዎችን እያሰፉ መሄዳቸው ለአህጉሪቱ አቪዬሽን እድገትና መጠናከር አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከናይጄሪያ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞችን መጨመር፣ የበረራ ቁጥር ማሳደግ፣ ወደ አዳዲስ መዳረሻዎች የመብረርና የመንገደኞችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም የቱሪዝም ገቢን ማሳደግ ላይ በትኩረት ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።
አየር መንገዱ እ.አ.አ ኖቬምበር 2025 ወደ ናይጄሪያ በረራ የጀመረበትን 65ኛ ዓመት ያከብራል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ከ65 በላይ መዳረሻዎች አሉት።
የናይጄሪያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዝደንት ካሺም ሼቲማ በቅርቡ በኢትዮጵያ ባደረጉት የስራ ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር ቁልፍ በሆኑ የሁለትዮሽ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።