በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት በተሰማሩ 562 ነዳጅ ማዳያዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል - ኢዜአ አማርኛ
በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት በተሰማሩ 562 ነዳጅ ማዳያዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት በመሰማራት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ችግር በፈጠሩ 562 የነዳጅ ማደያዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የነዳጅ ማዳያዎች፣ የነዳጅ አጓጓዦች እና ኩባንያዎች ጋር በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) እንዳሉት በሕገወጥ መንገድ ሰውሰራሸ የነዳጅ እጥረት በመፍጠር ችግር እየፈጠሩ ባሉ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባው ነዳጅ ለዜጎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴና ለኢኮኖሚ ወሳኝ የመሆኑን ያህል ያለአግባብ ለመክበር በነዳጅ ላይ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት የሚፈጥሩ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ሚኒስቴሩ ባደረገው ክትትል በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት ተሰማርተው ባገኛቸው 562 ነዳጅ ማዳያዎች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ጠቁመዋል።
ከ222 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ጠቅሰው፣ 54 ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው መጠየቃቸውንና በሕገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ መወረሱንም አንስተዋል።
በቀጣይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የነዳጅ ስርጭት በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚተገበር ገልጸው፥ ሕግን አክብረው በመስራት የሀገር ባለውለታ የሆኑ ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።
በዚህም በሀገሪቱ ነዳጅ እያቀረቡ ባሉት 60 የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ፥ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የጋራ ስራዎች ይተገበራሉ ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ሃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፥ በመዲናዋ የነዳጅ አቅርቦት ላይ በየቀኑ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በአግባቡ ሕዝቡን በማያገለግሉ አካላት እና ግብይቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማይፈጽሙት ላይ እየተወሰደ ያለው ሕጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በበኩላቸው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ ሥራ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፥ መንግሥት የነዳጅ ሪፎርም ካደረገ በኋላ በርካታ መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የነዳጅ አቅርቦት በ10 በመቶ መጨመሩን ጠቅሰው፥ ከአቅርቦት ጋር የተያያዘ ችግር አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
ነዳጅ ማጓጓዝን በተመለከተ በቀጣይ በተሻለ ሁኔታ በባቡር በብዛት የማጓጓዝ፣ የመሰረተ ልማት ሁኔታዎችን የማሻሻል እና የዘርፉ ተዋናዮች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በዘላቂነት የመፍታት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።