የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ የጀመረው በረራ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ የጀመረው በረራ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር ያግዛል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ የጀመረው በረራ ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎት ዘርፉ ከተመዘገቡ እድገቶች እና ውጤቶች መካከል አንዱ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሣምንት አራት ጊዜ ወደ ፖርቹጋል ፖርቶ ከተማ አዲስ በረራ ትናንት በይፋ አስጀምሯል።
አየር መንገዱ ወደ ፖርቶ ያደረገውን የመጀመሪያ የመንገደኞች በረራ አስመልክቶም ዛሬ በፖርቶ ከተማ የባለድርሻ አካላት የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የፓናል ውይይቱ በዋናነት የአየር መንገዱ የሚያደርገውን በረራ በኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር ላይ ያለመ ነው።
በፓናል ውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የፖርቶ አውሮፕላን ማረፊያ ዋና ዳይሬክተር ሩይ አልቬዝ፤ አየር መንገዱ የጀመረው በረራ ሁለቱ አገራትን በተለያዩ መስኮች ለማስተሳሰር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የዛሬው የፓናል ውይይትም በረራውን በካርጎ አገልግሎት ለማስተሳሰር ያላቸውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በውይይቱ በካርጎ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።
በፖርቶ አየር መንገድ ዋና የንግድ ኦፊሰር የሆኑት ካረን ስትራውጎ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ወደ ፖርቶ የጀመረው በረራ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን በስፔን በኩል አድርገን ከአውሮፓ ጋር ለመተሳሰር ያግዘናል ብለዋል።
ፖርቶ የኢንዱስትሪ ከተማ መሆኗን አንስተው፤ ከዚህ አኳያ አየር መንገዱ የጀመረው በረራ ከኢኮኖሚ ትስስር አንጻር ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍጥነት እያደገ ያለ ስመጥር አየር መንገድ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆኑት ጆን ጆርጅ ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለረዥም ጊዜ እንደሚያውቁት የሚናገሩት ጆን ጆርጅ፤ የአየር መንገዱ የፖርቶ በረራም ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር በፖርቹጋል የሚኖሩ ዜጎች ወደ ተለያዩ ሀገራት በቀላሉ እንዲጓዙ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዛሬ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በአገልግሎት ዘርፉ ከተመዘገቡ እድገቶች እና ውጤቶች መካከል አንዱ ማሳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን አንስተዋል።
አየር መንገዱ በተያዘው ዓመት ተጨማሪ 13 አውሮፕላኖችን በመግዛት አጠቃላይ የአውሮፕላን ብዛቱ 180 መድረሱን በመጠቆም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ ስድስት ተጨማሪ አዳዲስ መዳረሻዎችን በመጨመር አጠቃላይ ያላውን የመዳረሻ ብዛት ወደ 136 አሳድጓል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊዬን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።