የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ ነው - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ ነው - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል የዓለም አቀፉ ፖሊስ ድርጅት(ኢንተርፖል) ፕሬዚዳንት ሜጀር ጀነራል አህመድ ናስር አልራይዚን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው ውይት አድርገዋል።
ውይይታቸው ኢትዮጵያና ኢንተርፖል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል በኩል ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር ያከናወነቻቸው ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን በውይይታችን አንስተናል ብለዋል።
ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ በመከላከል ረገድ የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ እና የአቅም ግንባታ ትብብርን ለማስፋት የጋራ መግባባት መፈጠሩንም ተናግረዋል።
የኢንተርፖል ፕሬዝዳንት ሜጀር ጀነራል አህመድ ናስር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከኢንተርፖል ጋር ባላት ትብብር ውጤታማ እና ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።
ከውይይት በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በለውጡ ያከናወናቸውን ዘመናዊ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችንም ጎብኝተዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1958 ጀምሮ የኢንተርፖል አባል በመሆን በጋራ እየሰራች ነው።