በኢትዮጵያ የሰላም እና ጸጥታ ችግሮች ዋነኛ መንስኤ ስሁት የፖለቲካ ዕሳቤ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሰላም እና ጸጥታ ችግሮች ዋነኛ መንስኤ ስሁት የሆነ የፖለቲካ ዕሳቤ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የሰላምና ጸጥታ ችግር አንደኛው ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የስንፍና ፖለቲካ የወለደው ነው። በአገራችን የስንፍና ፖለቲካ ተንሰራፍቷል ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ግጭት ጠብ፣ተቃርኖን እየወለደ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ላብ አደር አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ደግሞ አውርቶ አደር ተጨምሯል ብለዋል።

እነዚህ ሰነፍ ፖለቲከኞች ስራ ሳይሰሩ፣ አገልግሎት ሳይሰጡ መብላት የሚፈልጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሌላኞቹ ክላሽ ካነገትኩ ፍላጎታቸውን የሚያሳኩ የሚመስላቸው እና በህዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይልና በወሬ እናፈርሳለን ብለው የሚያምኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት አትማሩ፣ ማዳበሪያ አትውሰዱ ብለው ዜጎችን የሚገድሉ ሰዎች ካሉ ይህ እኩይ ዓላማ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ስትጋጭ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ እሳት ጫሪ ጭልፊቶች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያውያንም እሳት ጫሪዎችን ማወቅና ማረም ያስፈልገናል፤ ያን ጊዜ ችግሩ ይፈታል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የማህበረሰቡን የሰላም ሚና በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፥ ማህበረሰቡ የታጠቁ አካላትን አትግደሉ፣ አትግደሉልኝ፣ እናንተም አትሙቱልኝ ማለት አለበት ብለዋል።

ልጆቼን ፈተና እንዳይፈተኑ እንዳይማሩ አትከልክሉ፣ እንዳንሰራ አታድርጉ፣ ማዳበሪያ እንዳይመጣ አታድርጉ ማለት አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንንም ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሰላም ፍላጎቱን አሳይቷል ብለዋል።

በመሆኑም ለህዝብ ጥያቄ የከበረ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ማንኛውም ሰው ወደ ስልጣን ሲመጣ ከዚህ ቀደም ምን ሰርተህ ታውቃለህ፣ ግብር ከፍለሃል ወይ፣ ማንን አገለገልክ፣ ታማኝ ነህ ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል በማብራሪያቸው።

ማህበረሰቡ የሰላምና የብልሹ አሰራር ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ሚናውን መወጣት እንዳለበት ገልጸው፤ ሰላም ሁል ጊዜ የሚገነባ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ግጭቶች ተፈትተው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ አንጻራዊ ሰላም ባይኖር ግብርናው፣ ማዕድኑ፣ ቱሪዝሙ አያድግም ነበር ሲሉ ጠቁመዋል።

አሁንም ቀሪ ችግሮችን በመፍታትና በጋራ በመስራት የሰላምን ዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ክልልን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም የፕሪቶሪያ ስምምንት የትግራይ ህዝብ ልጆቹን በየቀኑ ከማጣት ታድጓል ብለዋል።

ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሌሎች ሀገራት ደግሞ መንግስት ሰላም ይሻላል ብሎ ለተዋጉት ኃይሎች እድል ይሰጣል የሚል አዲስ ባህል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በክልሉ አገልግሎትን በሚመለከት ቴሌኮም፣ ባንኮች፣ አየር መንገድና ሌሎችም አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ጀምረዋል ብለዋል።

መንግስት ያልተመለሱ ተፋናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የጸና አቋም እንዳለው ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግስት ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በሰላም የመፍታት ፅኑ አቋሙን በተደጋጋሚ ማሳየቱን ገልጸው፤ የትግራይ ህዝብ ጦርነት ፈጽሞ አይፈልግም ሲሉ አብራርተዋል።

ሆኖም የዓለምን ሁኔታና የዘመኑን ውጊያ ባለመገንዘብ፣ መንግስት በተለያዩ ችግሮች ተወሯል፤ የሚያግዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን ነው በሚል ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ መኖራቸውን ተናግረዋል።

ይህ የተሳሳተ አካሄድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ትግራይ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ችግሮችን በውይይት በንግግር መፍታት ነው ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ ጦርነት እንዳይገባ አሁኑኑ የሰላም ሚናችሁን ተወጡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም