የዘንድሮው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ድሎች የተመዘገቡበት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ የዘንድሮው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ድሎች የተመዘገቡበት የማንሰራራት ዓመት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት፣ የግሉ ዘርፍ እንዲነቃቃ ምቹ ሁኔታ አለመኖር፣ የምርታማነት ውስንነት መኖርና በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ አለመኖር ለማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መነሻ መሆናቸውን አንስተዋል።  

ሪፎርሙ ከውጭ ባለን ትስስር ልናገኝና ልናጣ የምንችለውን በሀገር አቅም ልናገኝ የምንችለውን በለካ መንገድ የተቀመጠ ነውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የ8 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ተመዝግቦ እንደነበር በማውሳት፥ በዚህ ዓመት አጠቃላይ 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል ነው ያሉት።

ላለፉት ዓመታት 27 ሚሊየን በሴፍቲኔት የታቀፉ ተረጂዎች እንደነበሩ አንስተው፤ በግብርናው ዘርፍ በተሰራው ስራ ዘንድሮ 23 ሚሊዮን ዜጎችን ከሴፍቲኔት ተጠቃሚነት በራሳቸው አቅም ወደ መተዳደር መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

ይህ የማንሰራራት ትልቅ ማሳያ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም ቀሪዎቹን ከተረጂነት በማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ብርቱ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

የዘንድሮው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ የተጀመረበትና በሀገሪቱ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ድሎች የተመዘገቡበት መሆኑን አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በበጀት ዓመቱ 900 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረው፥ የዋጋ ግሽበትን አምና ከነበረበት 22 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 14 ነጥብ 4 በመቶ ማውረድ መቻሉንም ገልጸዋል።

ከወጭ ንግድ ከ8 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ የአገልግሎት ዘርፍ፣ ሬሚታንስ እና ሌሎች የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጮችን ጨምሮ በድምሩ 32 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ማስተናገዷን ገልጸው፥ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር በእጥፍ መጨመሩን አንስተዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ የአንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ የወዳጅነት ፓርክና ቤተ መንግስትን 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች የጎበኙ ሲሆን ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

በዓመት 600ሺህ ቶን መስታወት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ እየተገነባ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፋብሪካው ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚፈልገውን የመስታወት ምርት በጥራት ለማቅረብ የሚችል መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በቂ የመስታወት ፋብሪካ አልነበራትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃ ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀም ፋብሪካ መገንባት መጀመሯን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ኢትዮጵያ የጋዝ ምርቷን ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ እንደምትጀምርና የማዳበሪያ ፋብሪካ እንደምትገነባም ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም