የህዝበ-ሙስሊሙ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ይበልጥ መዋቅራዊ ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦የህዝበ-ሙስሊሙ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ይበልጥ መዋቅራዊ ስርዓትን የተከተለ  እንዲሆን እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የመረዳዳት ሥርዓቱን የተሳለጠ ለማድረግ የዘካ እና የአውቃፍ ኮሚሽን ዛሬ በይፋ ተመስርቷል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኮሚሽኑን ምስረታ በተመለከተ የውይይት መድረክ አካሒዷል፡፡


 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ተወካይ ሸህ ኢድሪስ አሊ፤ ዘካ ሰዎች ካላቸው በፐርሰንት ተቀንሶ አቅም ለሌላቸው የሚሰጥበት አግባብ ነው ብለዋል፡፡

አውቃፍ ሰዎች በገዛ ፈቃዳቸው ለማህበረሰብ አገልግሎት ለሚውሉ ጉዳዮች ስጦታ እንዲሰጡ የሚያደርግበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡


 

ይህ የዘካና የአውቃፍ ስርዓት ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ጊዜያዊ ችግርን ከማስታገስ ውጭ ዘላቂ ሃብትን በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳልነበረው ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ መመስረት ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት የሚያደርጓቸው ድጋፎች ህግ እና ስርዓት ተበጅቶላቸው ፤ዘመናዊ አሰራርን ተከትሎ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ለአገራዊ ልማት ትልቅ አቅም እንደሚሆንም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡለማዎች ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ጄይላን ኸድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዘካ እና አውቃፍ የእስልምና እምነት ምሰሶዎች ናቸው ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ መቋቋም የህዝበ-ሙስሊሙን የዘመናት ጥያቄ የሚመልስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በተበታተነ መንገድ ሲደረግ የነበረው የዘካ እና የአውቃፍ የአሰራር ስርዓት ዘመናዊ እንዲሆን ያደርጋልም ነው ያሉት።

በዘካና አውቃፍ ኮሚሽን ምሥረታው ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኘተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም