የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ በመጠበቅ ቴክኖሎጂን የታጠቀ በዕውቀት የሚመራ አስተማማኝ ሠራዊት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ በመጠበቅ ቴክኖሎጂን የታጠቀ በዕውቀት የሚመራ አስተማማኝ ሠራዊት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ በመጠበቅ ቴክኖሎጂን የታጠቀ በዕውቀት የሚመራ አስተማማኝ ሠራዊት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ገለጹ።
በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የኢፌዴሪ ዋር ኮሌጅ የብሔራዊ ደኅንነት ኮንፍረንስ፣ የምርምርና ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ዋና የዘርፉ ተዋናዮች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የአሸናፊነት አኩሪ ታሪክ የተጎናጸፈች ታላቅ ሀገር ናት ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትም የሀገር መከላከያ ሠራዊት የከፈለው አኩሪ ታሪክም በትውልድ ሲዘከር የሚኖር በደማቅ አሻራ የተፃፈ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የምርምርና ልማት ረቂቅ ፖሊሲም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቋማትን በተቀናጀ ሁኔታ ለመምራት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።
የ21ኛ ክፍለ ዘመን የጦርነት ሁኔታ ተቀያሯል ያሉት ሌተናል ጄኔራል ይመር፥ የመከላከያ የምርምርና ልማት ረቂቅ ፖሊሲም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በማካተት መዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ በመጠበቅ ቴክኖሎጂን የታጠቀ በዕውቀት የሚመራ አስተማማኝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የመከላከያ ምርምር ልማት ፖሊሲው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና የሳይበር ጦርነት አዝማሚዎችን ታሳቢ ማድረግ የቴክኖሎጂ የውጊያ አውዶችን ማየት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
የመከላከደ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ፥ የመከላከያ ሰራዊትን ሁለንተናዊ ለውጥ በስኬት መምራት የሚያስችሉ ጥናትና ምርምር ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላት ሴራ በሩቅ መመከት የሚችል አስተማማኝ የጦር መሳሪያና ቴክኖሎጂ የታጠቀ ሰራዊት መገንባቱን አስታውቀዋል።
በተመራማሪዎች የተዘጋጀው የመከላከያ ምርምርና ልማት ረቂቅ ፖሊሲም የሠራዊቱን የአሰራር ስርዓት በማዘመን የሠራዊቱን ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ተቋማት ወደ ስኬታማ የምርታማነት ምዕራፍ ተሸጋግረዋል ያሉት የኮሌጁ አዛዥ የመከላከያ ምርምርና ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ሠራዊቱ የደረሰበትን ደረጃ በማላቅ የውስጥና የውጭ ጸረ ሰላም ኃሎች ሊቃጡት የሚችለውን ጥቃት መግታት በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን እንስተዋል።
በመከላከያ ዋር ኮሌጅ የስትራቴጂያዊ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዲን ሥራው ደማስ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በመከላከያ ሰራዊት ተቋማት የሚያጋጥሙ ችግሮችንና መፍትሔዎቻቸውን የሚያትት ጥናትና ምርምር በማካሄድ ረቂቅ ፖሊሲው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በቀጣይ የምርምርና ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ወደ ትግበራ ሲገባ የሠራዊቱን ትጥቅ በራስ አቅም ከማሟላት ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ሚኒሊክ ዋለ(ዶ/ር) ረቂቅ ፖሊሲው የመከላከያ ሠራዊት ተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማሰናሰል በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በዝግጅት ሂደትም ከሀገር ውስጥ ተቋማትና ሌሎች ሀገራት ልምድና ተሞክሮ ተቀምሮበት በመከለከያ ሠራዊት ተቋማት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍትሔ መስጠት የሚያስች መሆኑን አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ተቋማትም የሚሰሯቸውን የጥናትና ምርምር የልማት ስራዎች በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ለማከናወን የተሻለ ግብዓት እንደሚሆን አንስተዋል።
የምርምርና ልማት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተሞክሮ፣ የተገኙ ውጤቶችና ተግዳሮቶች እንዲሁም የኢፌዴሪ መከላከያ የምርምርና ልማት ፖሊሲ ረቂቅ ዝግጅት ሂደቶችን የሚዳስሱ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።
የመድረኩ ተሳተፊዎችም በመከላከያ ዋር ኮሌጅ ቅጥር ግቢ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።