የከተማዋን ሰላም ከማፅናቱ በተጓዳኝ ውጤታማ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል

ባሕር ዳር፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፡- በባሕርዳር  በበጀት ዓመቱ የከተማዋን ሰላም ከማፅናቱ በተጓዳኝ  ውጤታማ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የከተማ  አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ጎሹ እንዳላማው አስታወቁ። 

የከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግስት ዕቅድ ሥራዎች አፈጻጸም ማጠቃለያ ግምገማና  የቀጣይ 90 ቀናት  ዕቅድ ላይ የመከረ መድረክ   ዛሬ በባሕርዳር  ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጎሹ እንዳላማው እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ የከተማዋን ሰላም ከማፅናት ጎን ለጎን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሥራዎችን በመፈጸም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

ይህም ከላይ እስከታች ያለው አመራር በመቀናጀት ሕብረተሰቡን በማስተባበርና በማሳተፍ  የመጣ  ነው ብለዋል።

የባህር ዳርና አካባቢውን ሰላም ከማፅናት ባለፈ የኮሪደር ልማትን በማሳለጥ ፅዱ፣ አረንጓዴ፣ ለኑሮ የበለጠ የተመቸች፣ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት መሰራቱን አስታውቀዋል።


 

በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማትም የከተማዋን የተፈጥሮ ፀጋና ውበት ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ ያስቻለ  መሆኑን ጠቁመው፤ ሕዝቡ ለሰላሙ መከበርና ለልማቱ እየሰጠ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በቀጣይ  በየተቋማቱ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥን  ይበልጥ አጠናክሮ   የሕዝብን እርካታ ለማረጋገጥ የቀጣይ ትኩረታቸው እንደሆነም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የባህር ዳር  ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው፤  በከተማዋ ሰላም እንዲሰፍንና የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ  በተደረገው ጥረት ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።


 

ሕብረተሰቡ ለከተማዋ ሰላም መጠበቅና ለልማት ስራዎች መፋጠን የበኩሉን መወጣቱን እንዲቀጥል አብሮ የመስራቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በባህርዳር ከተማ ዛሬ በተካሄደው መድረክ ላይም የከንቲባ ኮሚቴ አባላት፣ የክፍለ ከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም