ሰብአዊነትን በማስቀደም ሰላምና አብሮነትን በሚያጠናክሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ የህሊና እርካታ የሚሰጥ ነው - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሰብአዊነትን በማስቀደም ሰላምና አብሮነትን በሚያጠናክሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ የህሊና እርካታ የሚሰጥ ነው - ወጣቶች

ሠመራ፣ሰኔ 26/2017 (ኢዜአ) ፡- ሰብአዊነትን በማስቀደም ሰላምና አብሮነትን በሚያጠናክሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ ትልቅ የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ገለጹ።
"በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሐሳብ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ የተለያዩ ተግባራት ማከናወናቸውን እንደቀጠሉ ነው።
በዛሬው ዕለትም የአፋር ክልል የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሀገር ሰላም ፣ልማትና እድገት ያለው ሚና ላይ ያተኮረ ልምድ ለወጣቶቹ አካፍለዋል።
በዚህ ወቅት ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች እንዳሉት፤ ለሀገርና ለሕዝበ መስራት በጊዜና በቦታ የማይወሰን፤ ትልቅ የህሊና እርካታ የሚሰጥ ተግባር ነው።
ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣት አህመድ ዓሊ በሰጠው አስተያየት ፤ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የመተጋገዝና የመረዳዳት የዳበረ ባህል ያለን ሕዝቦች ነን ብሏል።
በተለይም ሰብአዊነትን በማስቀደም ሰላምና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ መሳተፍ ትልቅ ጥቅም እንዳለው በተግባር ማየቱን ተናግሯል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከማንም በላይ ተሳታፊውን ሰው የሚጠቅም መሆኑን በመረዳት በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታውን እየተወጣ መሆኑ እንደሚያኮራው ገልጿል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን የመጣው ወጣት አቡሽ ንጋቱ በበኩሉ፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ሰላምና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን እና በዚህም የህሊና እርካታ እንደሚሰጠው ተናግሯል።
ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ከፍ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ በታማኝነት ማገልገል እድለኝነት ነው፤ ከቀደሙ አባቶች መልካምነትን እና ትብብርን መውረስ ያስፈልጋል ብሏል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የዜግነት ግዴታ በመሆኑ በወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፏ ትልቅ የህሊና እርካታ እንደሰጣትና በዚህም ደስተኛ መሆኗን የተናገረችው ደግሞ ከጋምቤላ ክልል የመጣችው ወጣት ሮዛ ጳውሎስ ናት።
ከሐረሪ ክልል የመጣው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ሳሊህ እስክንድር፣ ሰብአዊነትን በማስቀደም ለሀገር ልማትና እድገት መስራት የሚያስደስት ተግባር መሆኑን ገለጿል።
ዛሬ በኃይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች የተሰጣቸው ምክርና የተካፈሉት ልምድ ይበልጥ የሚያበረታታቸው መሆኑን ገልጾ፤ ሰላምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እንድናጠናክር የሚረዳም ነው ብሏል።