በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ጥያቄዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን 268 ሚሊዮን ብር የመጠባበቂያ ፈንድ መቆጠብ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ጥያቄዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን 268 ሚሊዮን ብር የመጠባበቂያ ፈንድ መቆጠብ ተችሏል

ወላይታ ሶዶ፣ ሰኔ 26/2017 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄዎችን በራስ አቅም ለመመለስ በተሰራው ሥራ 268 ሚሊዮን ብር የመጠባበቂያ ፈንድ ለመቆጠብ መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
''ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለሀገር ሉዓላዊነትና ለተሟላ ክብር'' በሚል መሪ ሃሳብ ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተጀመረውን ሥራ ለማጠናከር ያለመ የአቅም ግንባታ ስልጠና በወላይታ ሶዶ ከተማ ተሰጥቷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) እንደገለጹት በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን በተሰራው ሥራ 268 ሚሊዮን ብር የመጠባበቂያ ፈንድ ማስቀመጥ ተችሏል።
አምና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ''ከተረጂነት ወደ ምርታማነት'' በሚል የተጀመረው ኢኒሼቲቭ በክልሉ ውጤት እያሳየ መሆኑንም አስረድተዋል።
ትርፍ በማምረት ለቤተሰብ ፍጆታና ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ የተለያዩ አደጋዎችን ተከትሎ ለሚነሱ የሰብአዊ ድጋፍ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።
ለአብነትም ባለፈው የመኸር ወቅት በክልሉ በ1 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ለምቶ ከተገኘው ምርት ውስጥ 25 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርትን ለዚሁ ዓላማ መዋሉን ተናግረዋል።
ዘንድሮም የእህል ክምችቱን ለማሳደግ ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፣ በክልሉ በ6 የክላስተር ማዕከላትና ዞኖች ላይ የእህል መጋዘን መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
አመራሩ በተፈጠረው ተግባቦት መሠረት ለሥራው ውጤታማነት በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክልሉ የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንደሀገር ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የተጀመረው ሥራ ከተረጂነት ለመውጣት እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
"በዚህ ልክ ከሰራን በአደጋ ጊዜ የሚያስፈልጉ ሰብዓዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ማሟላት እንችላለን" ያሉት አቶ ንጋቱ፣ ያለን አቅም አቀናጀቶ በጋራ የመስራቱ ጅምር መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምአ በበኩላቸው፣ ህዝቡን ከተረጂነት ለማውጣት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
ሰዎች ሰርተው የሚለወጡበትን አቅም በማሳደግ ከእርዳታ ጠባቂነት ለመውጣት የሚሰሩ ሥራዎች በቀጣይም ሊጠናከሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጬንቻ ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ ጬንቻ ጼራ ህብረተሰቡን ከተረጂነት ለማውጣት በአካባቢው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጊዶሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ወልደመድህን ካጫኖ በበኩላቸው ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት እና የአካባቢያቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከተረጂነት ለመውጣት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።