በተገነቡልን ተቋሟት የንጹህ መጠጥ ውሀ ችግራችን ተፈቷል-የበደኖ ወረዳ ነዋሪዎች

በደኖ፤ ሰኔ 26/2017 (ኢዜአ)፦  በተገነቡልን  ተቋማት  የንጹህ መጠጥ ውሀ  ችግራችን ተፈቷል ሲሉ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን  በበደኖ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በወረዳው ከተማና ገጠር ቀበሌዎች  ከ92 ማሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ሁለት የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማቱንም የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባዔ ኤልያስ ኡመታ እና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ መርቀዋል።


 

በበደኖ ወረዳ ኦዳ ቢሻን ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወይዘሮ ማሾ መሀመድ በሰጡት አስተያየት፤  ቀደም ሲል በአካባቢው የውሃ ተቋም  ባለመኖሩ ከርቀት አካባቢ በመቅዳት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ያጠፉ እንደነበር ተናግረዋል።

አሁን ላይ በአካባቢያቸው የተገነባው የውሃ ተቋም ለአገልግሎት በመብቃቱ ችግራቸው መፈታቱን ገልጸዋል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋሙ ከውሀ ወለድ በሽታዎች እንደሚታደጋቸውም ተናግረዋል። 


 

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ አብደላ አባስ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል የውሃ ተቋም ባለመኖሩ ለመጠጥና ለከብቶች የሚሆን  ውሃ ለማግኘት ረጅም ርቀት ይጓዙ እንደነበር   አስታውሰዋል።

ይህም በግብርና ስራቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመው አሁን ላይ መንግስት የገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ  የቆየ ጥያቄያቸውን  መመለሱን  ገልፀዋል።


 

የበደኖ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ራዚያ አብዱላሂ በበኩላቸው በከተማው ተገንብቶ  በየቀበሌው የተዳረሰው የንፁህ መጠጥ ውሃ  ችግሩን መቅረፉን  አመልክተዋል።


 

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ውሃና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል ሀሰን፤ በበጀት ዓመቱ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ 55 አዳዲስ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅተዋል።


 

በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በተከናወነው የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ  90 ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ በበኩላቸው የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች የመመለስ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

መሰረተ ልማቶችን በፍጥነትና በጥራት ገንብቶ ለአገልግሎት የማብቃት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም