የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንግስት የፀና አቋም አለው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንግስት የፀና አቋም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በስብሰባው የመንግስትን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት ስምምነቱ ለትግራይ ህዝብ እፎይታ አምጥቷል።

ልጆቻቸውን በየቀኑ ከማጣት ታድጓል፤ ለኢትዮጵያ እና ለበርካታ ሀገራት ልምድ የሚሆን አዲስ የፖለቲካ ባህል አምጥቷል ብለዋል።

አገልግሎትን በተመለከተ በወቅቱ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ መንግስት የተቋቋመበት ሁኔታ ስምምነቱ ማመቻቸቱን ገልጸዋል።

በራያና ፀለምት ያሉ ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ መመለሳቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የስምምነቱ ውጤት ነው ብለዋል።

የወልቃይት ተፈናቃዮች የመመለስ ስራ መስራት እንዳለበት አንስተው፤ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንግስት የፀና አቋም እንዳለውም አረጋግጠዋል።

ለዚህም በሁሉም ወገን ያሉ አካላት ተባባሪ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የታጣቂዎች ተሃድሶ ተፈፃሚ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ያለው ፍላጎት ልማት እና ልማት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልፀዋል።

የትግራይ ሕዝብ ጦርነት ፈጽሞ አይፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም የዓለምን ሁኔታና የዘመኑን ውጊያ ባለመገንዘብ፣ መንግስት በተለያዩ ችግሮች ተወጥሯል፤ የሚያግዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን ነው በሚል ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ አሉ። ይህ የተሳሳተ አካሄድ ነው ብለዋል።

ትግራይ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ችግሮችን በውይይት፣ በንግግር መፍታት እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ ጦርነት እንዳያመራ አሁኑኑ የሰላም ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

መንግስት አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለውም ፍላጎታችን ማልማት ነው ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም