በሰቆጣ ከተማ ሰላምን ከመጠበቅ ጎን ለጎን የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ ነው

ሰቆጣ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፡-በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ሰላምን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ በሰልፍ ላነሳው የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው ህብረተሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ሥራ በመሰራቱ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ተችሏል። 

የተረጋገጠውን ሰላም በመጠቀም ህብረተሰቡ በህዝባዊ ሰልፍ የጠየቀውን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለእዚህም የከተማው ነዋሪዎች የረዥም ጊዜ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየው የሰቆጣ-ብልባላ-ላልይበላ-ጋሸና የአስፋልት መንገድ ሥራ በአሁኑ ወቅት መጀመሩ በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጠቀሜታ ያላቸው ከ19 በላይ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ የከተማው ነዋሪዎች በህዝባዊ ሰልፍ ላነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አስተዳደሩ የጀመረውን ጥረት እንደሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ አመራር የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ መሰረት ያደረገ እቅድ በማውጣት ተጨማሪ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ይሰራል ብለዋል።

የሰላምና የልማት ሥራዎች ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆናቸው በየአካባቢው ህብረተሰቡን ያሳተፉ የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑም ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል። 

"ህዝቡ ፍላጎቱ ሰላምና ልማት እንደሆነ በሰላማዊ ሰልፍ ደጋግሞ ጠይቋል" ያሉት አቶ ጌትነት፣ በጫካ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሀይሎችም የመንግስትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው እንዲመጡ ህዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ባለፈው እሁድ ሰላምና ልማትን የሚደግፍ እና ጽንፈኝነትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ ማካሄዳቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም