ቀጥታ፡

በተያዘው ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ህፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ በተያዘው ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ህፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትምህርት ጋር በተያያዘ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ቅድመ መደበኛ ላይ ትኩረት ተደርጎ  እየተሰራ ይገኛል።

4 ነጥብ 2 ሚሊየን ህፃናት በቅድመ መደበኛ ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ከነዚህም መካከል 29 ሺህ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት መሆናቸው ተናግረዋል።

የመምህራን ስልጠና በሚመለከት በማስተማር ስነ ዘዴና በሚያስተምሩት ትምህርት ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ገልፀዋል።

በዚህም ባለፈው በጀት አመት ለ68 ሺህ መምህራን ስልጠናው እንደተሰጠ አስታውሰው፤ በዘንድሮው በጀት አመት ለ80 ሺህ መምህራን በቀጣይ ስልጠና እንደሚወስዱ ጠቅሰዋል።

ይህም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በእጅጉ ያግዛል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ትምህርት ሚኒስቴር 30 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየገነባ  ነው ብለዋል።

በተጨማሪም 46 ሚሊየን የመማሪያ መጽሃፍት ታትሞ ለሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም