ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተፋሰሱ አገራት እንዲገኙ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተፋሰሱ አገራት እንዲገኙ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦የተፋሰሱ አገራት በመስከረም ወር በሚመረቀው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስነ-ስርዓት ላይ እንዲገኙ እና የጋራ ተጠቃሚነትን በተግባር እንዲመለከቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስብሰባው የመንግስትን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።
የሃይል አቅርቦትና ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላት የጋራ ተጠቃሚነት አቋም የጸና መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከተፋሰሱ አገራት ጋር በጋራ የመልማት፣የማደግና የመበልጸግ እቅድን ነድፋ እየሰራች መሆኗን ጠቁመዋል።
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥያቄ ካላቸው አገራት ጋር ግልጽ ውይይት ለማድረግ አሁንም በሯ ክፍት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ገለጸዋል።
በብዙ ልፋትና መስዋእትነት የተገነባው ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ በቅርቡ በመስከረም ወር እንደሚመረቅም ተናግረዋል።
በመሆኑም የተፋሰሱ አገራት በዚህ ታላቅ ቀን እንዲገኙና የጋራ ተጠቃሚነትን በተግባር እንዲመለከቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።