ተማሪዎች በሀገር ልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ሊያጠናክሩ ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
ተማሪዎች በሀገር ልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ሊያጠናክሩ ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ ፤ ሰኔ 26/2017 (ኢዜአ)፡- ተማሪዎች በሀገር ልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያው ዙር የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
ርዕሰ መስተዳድሯ አለሚቱ ኡሞድ፣ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት ተማሪዎች በሀገሪቱ የልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።
መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶች ለማሳደግ በሚያደረገው ጥረት የተማሪዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዛሬ በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ጋር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ይህንኑ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎችም በክረምቱ የእረፍት ጊዜያቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ የአካባቢያቸውን ህዝብ ማገልገል እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ድሪባ ኢቲቻ (ዶ/ር) በቡኩላቸው የ2017 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያው ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎቹም ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማከናወናቸው በሀገር ልማት አሻራቸውን የሚያሳርፉበትን እድል ማስፋቱን ገልፀዋል።
ከተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች መካከል ተማሪ ላትጆር ቱትና ተማሪ ኮንግ ጆክ በሰጡት አስተያየት ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ላይ መሳተፋቸው ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሚና የሚያበረክቱበትን አጋጣሚ መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ዛሬ በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ የጀመሩቱን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱም ወጣቶችን በማስተባበር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።