ቀጥታ፡

በዓመት 600 ሺህ ቶን መስታወት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ እየተገነባ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በዓመት 600 ሺህ ቶን የማምረት አቅም ያለው የመስታወት ፋብሪካ እየገነባች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው።

የምክር ቤቱ አባላት በፖለቲካ፣ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲ እና በሌሎች ጉዳዮች ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለተነሱላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች በመሆኑ በዘርፉ ዕድገት እየተመዘገበ ነው።

በተለይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎች ማምረት አቅም በማሻሻል ቀድሞ ከነበረበት ከ47 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማደጉን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም እየተገነቡ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዓመት 600 ሺህ ቶን መስታወት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ እየገነባች መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ፋብሪካው ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚፈልገውን የመስታወት ምርት በጥራት ለማቅረብ የሚችል መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በቂ የመስታወት ፋብሪካ አልነበራትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን የአገር ውስጥ ጥሬ እቃ ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀም ፋብሪካ መገንባት መጀመሯን ተናግረዋል።

መንግስት የኢንዱስትሪ ምርቶችን ምርታማነት ለማጠናከር የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማምረት አቅም ለመጨመር ትኩረት መስጠቱንም ተናግረዋል።

በጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ላይ መሆኗን የሚያሳዩ ታላላቅ ድሎች የተመዘገቡበት መሆኑን አንስተው፤ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚቀርብ ኢነርጂ 40 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም