ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት የማምረት አቅም አምና ከነበረበት 59 በመቶ ዘንድሮ 65 በመቶ ደርሷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት የማምረት አቅም አምና ከነበረበት 59 በመቶ ዘንድሮ 65 በመቶ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ኢንዱስትሪን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ዘንድሮ 12 በመቶ ገደማ ዕድገት ለማምጣት ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ንቅናቄ በጣም ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም የማምረት አቅም አምና 59 በመቶ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ 65 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

ይህም የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ ነው ያሉ ሲሆን በዚህ ዓመት የኢንዱስትሪው የኃይል ፍላጎት በ40 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት።

ይህ ትልቅ ዕድገት ነው፤ የሲሚንቶ ምርት ከፍ ብሏል፤ በብረት ውጤቶች 18 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ብረት የማምረት አቅም መገንባቷን ጠቁመው የብረት ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ ማሟላት የሚያስችሉ ስራዎች ተጀምረዋል ነው ያሉት።

የመስታወት ፋብሪካ በዓመት 600ሺህ ቶን ገደማ የሚያመርት እየተገነባ መሆኑን ገልጸው የፋብሪካው ስራ በማንኛውም መስፈርት አስደናቂ ነው ብለዋል።

በሚቀጥለው ታህሳስ ወይም ጥር ላይ እንደሚጠናቀቅ ጠቅሰው የሶላር ምርት ፓናል ምርት የሚያመርት ፋብሪካዎችም እየተገነቡ መሆኑና በቅርቡ ይመረቃሉ፤ ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት እየሰራን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም