ቀጥታ፡

ዘንድሮ 23 ሚሊዮን ዜጎች ከሴፍቲኔት ተጠቃሚነት ነፃ ወጥተዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ዘንድሮ 23 ሚሊዮን ዜጎች  ከሴፍቲኔት ተጠቃሚነት ነፃ መውጣታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ እቅድ አፈጻጸም ከቁልፍ የኢኮኖሚ እድገት አመላካቾች አንጻር በምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለው ጥያቄ ለአባላቱ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ነው።

የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት፣ የግሉ ዘርፍ እንዲነቃቃ ምቹ ሁኔታ አለመኖር፣ የምርታማነት ውስንነት መኖርና  በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ አለመኖር ለማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መነሻ መሆናቸውን አንስተዋል።   

ይህ ስራ በኢትዮጵያ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን አለም ላይ የነበረውን የኢኮኖሚ ሁኔታም ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

የአለም የንግድ ስርዓት መዋዠቅ መኖሩን ጠቅሰው በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአለም እድገት 3 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ይኖራል ተብሎ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ 2 ነጥብ 8 ሊሆን እንደሚችል መገመቱን ገልፀዋል።

ከሰሃራ በታች ባሉ አገራትም 4 ነጥብ 2 እድገት ይኖራል ተብሎ የተገመተ ሲሆን 3ነ ጥብ 8 እንደሚሆን አስቀምጧል።

ወደ አፍሪካ የሚፈሰው እርዳታ ዘንድሮ 7 በመቶ መቀነሱንና በቀጣይ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚችል ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከውጭ ባለን ትስስር ልናገኝና ልናጣ የምንችለውን በአገር አቅም ልናገኝ የምንችለውን በለካ መንገድ የተቀመጠ ነውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለፈው አመት የ8 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ተመዝግቦ ነበር አጠቃላይ 8 ነጥብ 4 ለማምጣት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል ነው ያሉት።

ግብርና የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ዋልታ የሆነና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ላለፉት አመታት 27 ሚሊየን በሴፍቲኔት የታቀፉ ተረጂዎች እንደነበሩ አንስተው፤ በግብርናው ዘርፍ በተሰራው ስራ ዘንድሮ 23 ሚሊዮን ከሴፍቲኔት ተጠቃሚነት ነፃ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ይህ የማንሰራራት ትልቅ ማሳያ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም ቀሪዎቹን ከተረጂነት በማላቀቅ ኢትዮጵያን ከምግብ ተረጂነት በማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ብርቱ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሊታረስ የሚችል ሰፊ መሬት ካላቸው አገራት መካከል መሆኗን አንስተው አምና 26 ሚሊየን ሄክታር መሬት ታርሶ እንደነበርና ዘንድሮ 31 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ማረስ መቻሉን ተናግረዋል። 

አምና በሁሉም አይነት የሰብል ምርቶች ኢትዮጵያ የሰበሰበችው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኩንታል ምርት እንደነበር ጠቅሰው ዘንድሮ 1ነጥብ 5 ቢሊየን ኩንታል መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።።

ይህም 24 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ያለው መሆኑን ነው ያስረዱት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም