የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖ ምርቶች የጥራትና ደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ ቁጥጥር እየተደረገ ነው -የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖ ምርቶች የጥራትና ደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ ቁጥጥር እየተደረገ ነው -የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን
አዳማ ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፡- የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖ ምርቶች የኢትዮጵያን የጥራትና ደህንነት መስፈርት እንዲያሟሉ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ የምግብ ምርት ጥራትና ደህንነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከስጋ፣ ከወተትና እንቁላል አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በጥራት ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የምግብ ምርቶች ጥራትና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖ ምርቶች የኢትዮጵያን የጥራትና ደህንነት መስፈርት ያሟሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርበው ምርት ጥራትና ደህንነቱን የጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ እንዲሁም ወደ ውጭ ሀገራት የሚላክ ምርትም መስፈርት ያሟላ መሆኑን ፍተሻ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም ወደ ውጭ የሚላኩ የስጋ ምርቶችን የሚያቀነባብሩ 11 ዘመናዊ የኤክስፖርት ቄራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ መሆናቸው እየተረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘርፉ እንደ ክፍተት ከሚነሱ ችግሮች መካከል በኤክስፖርት ቄራዎች አካባቢ በሚፈለገው መልኩ የማስፋፊያ ስራ ያለመከናወኑ፣ የአካባቢ ጥበቃና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።
ከዚህም ባለፈ በወተት ምርት ላይ የሚታየውን የጥራትና ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንካራ የጥራትና ቁጥጥር ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑንም አክለዋል።
በባለስልጣኑ የእንስሳት ምርት ሬጉላቶሪ መሪ ስራ አስፈፃሚ አያሌው ሹመት (ዶ/ር) በበኩላቸው የእንስሳት ምርት አያያዝ፣ ጥራትና የአጓጓዝ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ በእንስሳት፣ በዶሮ፣ በንብና ዓሣ የምርት ጥራት እና ደህንነት የተረጋገጠ እንዲሆን የዘርፉን ተዋናዮች ያሳተፈ የቁጥጥር ስራ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።