በክልሉ ያልተጠናቀቁ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ህብረተሰቡን በማስተባበር ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ያልተጠናቀቁ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ህብረተሰቡን በማስተባበር ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው
ቦንጋ ፤ሰኔ 26/2017 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ያለውን ውስን ሃብት በመጠቀምና ህብረተሰቡን በማስተባበር ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢነጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለፁ።
በክልሉ ግንባታው ዘግይቶ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲነሳበት የነበረው የአውራዳ ኢንደስቲሪያልና ኮንስትራክሽን ኮሌጅ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ በቅቷል።
በምረቃው መርሃ ግብር ላይም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት ያለውን ውስን ሃብት በመጠቀምና ህብረተሰቡን በማስተባበር ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
የአውራዳ ኢንዱስትሪያልና ኮንስትራክሽን ኮሌጅም አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ የአካባቢውን ፀጋ መሰረት ባደረጉ የስልጠና መስኮች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ዐቢይ አንደሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ 20 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ኮሌጆቹ በአዲሱ የለውጥ እሳቤ ፈጠራን፣ ቴክኖሎጂን፣ ክህሎትንና የምርምር ብቃትን መሰረት ያደረገ ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት የበቃ የሰው ኃይል የማፍራት ተልእኮን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአውራዳ ኢንዱስትሪያልና ኮንስትራክሽን ኮሌጅ ዲን አቶ እዮብ መንገሻ በበኩላቸው ኮሌጁ የራሱ ሕንፃ ሳይኖረው ከሶስት ዓመት በፊት በአውራዳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር እንደነበረ ገልፀዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በመማር ማስተማር ስራው ላይ እንቅፋት ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን የኮሌጁ ግንባታ መጠናቀቅ ችግሩን እንደሚፈታው ተናግረዋል ።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ መላኩ መኩሪያና አባ ጴጥሮስ አበበ ኮሌጁ ተመርቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኮሌጁ ግንባታ ሳይጠናቀቅ ለዓመታት መዘግየቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ለቅሬታ ዳርጎት እንደነበር ገልፀው፣ አሁን ለምረቃ በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የአውራዳ ኢንዱስትሪያልና ኮንስትራክሽን ኮሌጅ በ2007 የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም በተለያየ ምክንያት ግንባታው ዘግይቶ ቆይቶ አሁን ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡