የአፍሪካ አህጉራዊ የኃይል ቋት ስርዓትን የመፍጠር ግብ በትክክለኛ ምዕራፍ ላይ ይገኛል - የአፍሪካ ህብረት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አህጉራዊ የኃይል ቋት ስርዓትን  የመፍጠር ራዕይ በትክክለኛ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ።   

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማት እና ኢነርጂ ዳይሬክተር ካሙጊሻ ካዛውራ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና አካል የሆነው አህጉራዊ ነጠላ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ ዘላቂ የኃይል ልማት ማረጋገጥን አላማ ያደረገ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የተቀናጀ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ በመፍጠር በአፍሪካ በመኖሪያ ቤቶች፣ በንግድ ተቋማት እና ኢንዱስትዎች ዘላቂ፣ ተአማኒ፣ ተወዳዳሪ እና ተመጣጣኝ ኢነርጂ ማቅረብ እንደሚያስችል አመልክተዋል። 

በዚህ ረገድም የአፍሪካ ሀገራት ከጎረቤቶቻቸው ጋር ትስስር ለመፍጠር እየተገበሯቸው ያሉ ፕሮጀክቶችን አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ጋር የፈጠረችው የኃይል መስተጋብር የአፍሪካ ነጠላ የኤሌክትሪክ ኃይል ትግበራ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት አካል መሆኗን ገልጸው ቋቱ ሀገራትን በማስተሳሰር ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ። 

ኬንያ ከታንዛንያ ጋር የኃይል ስርዓቷን ለማስተሳሰር እያከናወነች እንደምትገኝና ይህም በቀጣይ ከደቡባዊ አፍሪካ የኃይል ቋት የኤሌክትሪክ ግብይት ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በቀጣይ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋትን ከደቡባዊ አፍሪካ የኃይል ቋት ጋር የማገናኘት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ አህጉራዊ ነጠላ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያው  ውሃ፣ ፀሐይ፣ ንፋስ እና የታዳሽ ኃይሎችን ጨምሮ ለሁሉም የኃይል ምንጮች ትኩረት እና እውቅና የሚሰጥ ነው።

የኃይል አማራጮቹ የአፍሪካ የኃይል ስርዓት ማስተር ፕላን አካል እንደሆኑ ገልጸው ይህም አህጉራዊ ነጠላ የኤሌክትሪክ ኃይልን እውን ለማድረግ የሚያስችል ቁልፍ ምሰሶ መሆኑን አመልክተዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና የዓለም ባንክ ግሩፕ ጋር በመሆን በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት “Mission 300” የተሰኘ ኢኒሼቲቭ ይፋ ያደረጉ ሲሆን ኢኒሼቲቩ ለአፍሪካውያን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ማስፋትን ያለመ ነው።

ኢኒሼቲቩ እ.አ.አ በ2030 300 ሚሊዮን የአፍሪካ ዜጎችን በኤሌክትሪክ የማስተሳሰር ውጥን አለው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የጀርመን መንግስት እና ሌሎች የልማት አጋሮች ለኢኒሼቲቩ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። 

የአፍሪካ ነጠላ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የኢነርጂ ደህንነትን እና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ተወዳዳሪነትን የማሳደግ እቅም እንዳለው ታምኖበታል።
 #Ethiopian_News_Agency #Ethiopia #ኢትዮጵያ #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም