በአማራ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል

ባህርዳር ሰኔ 25/2017 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት፤ ለክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተደረገውን አጠቃላይ ዝግጅት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርጋ ግብር ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል 20 ሚሊዮን የሚሆነው የቡና እና ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ለችግኝ ተከላው ቀደም ብሎ መሬት በመለየት የጉድጓድ ቁፋሮ እና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አንስተው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አሻራውን ለማኖር እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ በይፋ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልልም ተጀምሯል።
በክልሉ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞንና በባህርዳር ከተማ አስተዳደር የችግኝ ተከላ መከናወኑን አስታውሰው በሌሎች አካባቢዎችም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር ገደፋዬ ሞገስ እና በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የጓጉሳ ወረዳ አርሶ አደር አለማሁ አድማስ፤ የተራቆቱ አካባቢዎችን በመትከልና በመንከባከብ የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ጥቅሙን በአግባቡ በመረዳቸው በዘንድረው የክረምት ወቅትም የሚተክሏቸውን ችግኞች በባለቤትነት ተንከባክበው ለማሳደግ መዘጋጀታቸው አስታውቀዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከሉት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ከ82 በመቶ በላይ መፅደቁን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።