በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ-ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 25/2017(ኢዜአ):-በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሚቀጥሉት አስር ቀናት ለክረምት ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ እየተስፋፉና እየተጠናከሩ ይቀጥላሉ።

በደቡብ ምዕራብ፣ምዕራብ፣ሰሜን ምዕራብ፣ሰሜን፣ መካከለኛው እና ሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖር አሃዛዊ የትንበያ መርጃዎች እንደሚያሳዩ ተጠቁሟል።

በተለይ በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብና መካከለኛ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ብለዋል።

አልፎ አልፎ በውሃ አካላትና አካባቢ በምዕራብ፣ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅ እና መካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል ገልጸዋል።

በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ነጎድጓዳማና በረዶ አዘል ዝናብ እና የዝናቡ ጥንካሬም ለረጅም ሰዓታት ያለማቋረጥ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በመግለጫው ተመላክቷል።

በክረምቱ ወቅት የሚዘንበው ዝናብ በአመዘኙ አዎንታዊ ሚና የሚኖረው መሆኑ ተገልጿል።

ይህም አስቀድሞ ለተዘሩ ሰብሎች፣ ለመኽር ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎችና የጓሮ አትክልት የውሃ ፍላጎት ለማሟላት በኩል መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።

አብዛኛው የአገሪቱ ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ የገጸ ምድር የውሃ ፍሰት ይኖራቸዋል፤ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚኖረው ከባድ ዝናብ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል በመጪው አስር ቀናት የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት በአፋር፣ በምስራቅ አማራ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ምዕራብ እና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ሥፍራዎች ላይ ከ26 እስከ 41 ዲግሪ ሴልሺዬስ በላይ ሙቀት እንደሚኖራቸው ትንበያው ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም