የአየር ኃይል ሶስተኛ አየር ምድብ የስፖርት ውድድር ተጠናቀቀ

ድሬዳዋ፣ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦በኢፌዴሪ አየር ኃይል ሶስተኛ አየር ምድብ ለሁለት ሳምንት ሲካሄድ የሰነበተው የስፖርት ውድድር ማምሻውን ተጠናቀቀ።

በምድቡ ከሰኔ 11 ቀን 2017 ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ሲካሄድ የሰነበተው ውድድር ዛሬ ማምሻውን በተደረገ የእግር ኳስ ጨዋታ ተጠናቋል ።

በወንዶች በተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ የሶስተኛ አየር ምድብና የሆርሞድ ጤና ቡድን መደበኛውን የጨዋታ ጊዜ ያለምንም ጎል ተለያይተዋል።

አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡ የፍፁም ቅጣት ምቶች ሆሮሞድ አራት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸናፊ ሆኗል።

ከወንዶች እግር ኳስ በተጨማሪም በምድቡ የተለያዩ ክፍሎች መካከል የአትሌቲክስ፣ የመረብ ኳስ ፣የእጅ ኳስና ሌሎች ውድድሮች በሁለቱም ፆታ የተካሄዱ ሲሆን ለአሸናፊዎቹ ሽልማት ተበርክቷል።

ለአሸናፊዎች የተዘጋጀውን የዋንጫና ሌሎች ሽልማቶች የሰጡት የኢፌድሪ አየር ኃይል ሶስተኛ ምድብ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ቡሽሬ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።

ዋና አዛዡ ኮሎኔል ደረጀ ቡሽሬ በወቅቱ እንደተናገሩት፥ ስፖርት የሠራዊቱን አካላዊ ብቃትና ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ በማዳበር የትኛውንም ግዳጅ በታላቅ ብቃት እንዲወጣ እያገዘ ይገኛል ።

እየተጠናቀቀ በሚገኘው በጀት አመት ምድቡ በተለያዩ ተልዕኮዎቹ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑንም ጠቅሰዋል።

በውድድሩ የከተማው አምስት የጤና ቡድኖች መሳተፋቸው ሠራዊቱ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ትስስር እንዲጠናከር አጋጣሚ የተፈጠረበት መሆኑን አንስተዋል ።

ዛሬ ማምሻውን በተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ የከተማው የስፖርት ቤተሰቦች በስፍራው ተገኝተው ውድድሩን ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም