በአረንጓዴ አሻራ በንቃት በመሳተፍ ሌሎች የማህብረሰብ ክፍሎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ እንሰራለን -የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦በእረፍት ጊዜያቸው ወደ ተመረጡበት አካባቢ ሲሄዱ በአረንጓዴ አሻራ በንቃት በመሳተፍ ሌሎች የማህብረሰብ ክፍሎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ አበክረው እንደሚሰሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ሰኔ 20/2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ይሆናል።

ይህንን ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር መካሔድ ጀምሯል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አረንጓዴ አሻራን አስመልክቶ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየትም ዜጎች በአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር በመሳተፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገውን ጥረት የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። 

ዜጎች በአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር  እያደረጉ ያለውን ተሳትፎ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አባላቱ በእረፍት ጊዜያቸው ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን በአካባቢያቸው በአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር  የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አዲሷ አሰፋ እንደገለጹት፤ ችግኝ መትከል ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተጨማሪ ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

በመሆኑም ማህበረሰቡ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ  በማጠናከር ውጤቱን ማሳደግ እንደሚገባም  አመልክተዋል፡፡  


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ስራ ስምሪትና  ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ኡስታዝ ካሚል አሊ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራ ለሁለንተናዊ አገራዊ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ዜጎች በአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር ላይ ተሳትፏቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ በቀጣይ ወደ ተመረጡበት አካባቢያቸው ሲመለሱ ከተጣለባቸው ኃላፊነት ጎን ለጎን ህዝቡ በአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር ይበልጥ ተሳትፎ እንዲጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።


 

በምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጌ ቁፋ አረንጓዴ አሻራ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ተመናምኖ የቆየውን የደን ሃብት ወደ ነበረበት በመመለስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

በመሆኑም ህዝቡ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ያለውን ተሳትፎ እንዲጨምር ህዝቡን በማስተባበርና አብሮ በመትከል አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።


 

ባለፉት አመታት በተከታታይ ተግባራዊ በተደረገው በአረንጓዴ አሻራ  መረሃ-ግብር እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን ዘላቂ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው ያሉት ደግሞ በምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሙሉነሽ ነሞሬ ናቸው።

በመሆኑም ማህበረሰቡ ለአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር ያለውን ተነሳሽነት በመጨመር ያለውን ተሳትፎ እንዲያጎላ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም