ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምግብና መድሃኒት ደህንነትና ጥራት ምርመራ አቅም እየገነባች ነው-ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምግብና መድሃኒት ደህንነትና ጥራት ምርመራ አቅም እየገነባች ነው-ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 25/2017(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተረጋገጠ የመድሀኒትና የምግብ አቅርቦትን ለማስፋት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ላብራቶሪና የጥራት ምርመራ ስርዓትን እያስፋፋች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ከዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን ቦርድ አይሶ 17025/2012 በመድሃኒት ጥራት ምርመራና የህክምና መገልገያ መሳሪያ ጥራት ምርመራ ያገኘውን እውቅና ይፋ አድርጓል።
የእውቅና መርሃ-ግብሩን አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ባስተላለፉት መልእክት መንግስት ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እያከናወነ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ደህንነቱ የተረጋገጠ የመድሃኒትና የምግብ አቅርቦትን ለማስፋት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ላብራቶሪና የጥራት ምርመራ ስራም የትኩረት አቅጣጫ ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
በዚህም ውጤት መመዝገቡን ያነሱት ሚኒስትሯ በሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ተአማኒ የሆኑ የህክምና መሳሪያና የምግብ ምርመራ ስርዓትን መዘርጋት እንደተቻለ አስታውቀዋል።
ይህም በህክምናው ዘርፍ የነበሩ ጉድለቶችን ለማረምና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት አስቻይ ሁኔታን መፍጠሩን አመልክተዋል።
የተፈጠረው አስቻይ ሁኔታ በጤናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ሀገራዊ ስኬት ለማስቀጠል አይነተኛ ሚና እንዳለው ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የተሰጠው እውቅና በዘርፉ ለጥራት ፍተሻ የተሰጠውን ትኩረት የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቀጣይም ይህን መሠል የጥራት ፍተሻ ስራ ለጤናው ዘርፍ ውጤታማነት ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ በበኩላቸው፥ ተቋሙ የተለያዩ የለውጥ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ የምግብና ጤና ግብአቶች ጥራት፣ የቁጥጥር ስራውን በቴክኖሎጂ መደገፍና የሰው ኃይል ልማት ስራ በሪፎርሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።
የተካሄደው ሪፎርም ኢትዮጵያ በዘርፉ የአፍሪካ የልህቀት ማእከል እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በቅርቡ ከዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን ቦርድ አይሶ 17025/2012 በመድሀኒትና በህክምና መሳሪያ ደህንነትና ጥራት ቁጥጥር እውቅና መገኘቱ ለተሻለ ትጋትና ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡