በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቡን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው -- ርእሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 25/2017 (ኢዜአ) --በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቡን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም በጀት ማከፋፈያ ቀመር ሂደት ላይ ተግባቦት ለመፍጠር ያለመ  የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል፡፡


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እና የልማት ተጠቃሚነትን  ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው።

የክልሉን ህዝብ አዳጊ ፍላጎቶችን ለማሟላት እና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በበጀት ቀመር ላይ ተግባቦት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በዚህም የ2018 ዓ.ም በጀት ከመወሰኑ በፊት ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰቡ መረጃዎችን  መሰረት በማድረግ የበጀት ቀመሩን  ለመስራት   መግባባት ላይ መድረስ  በማስፈለጉ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት በበጀት ቀመሩ ላይ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማከናወኑን ጠቅሰው መግባባት የተደረሰበት መረጃ ለክልሉ ምክር ቤት ይቀርባል ብለዋል፡፡


 

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አዳማ ቲምጳዬ በበኩላቸው በ2018 በጀት ዓመት ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መረጃዎችን የማደራጀት ስራ መሰራቱን  ገልጸዋል።

መድረኩ በሁሉም መዋቅር አመራሮች ዘንድ ግልጽነትና መግባባት በመፍጠር  የኢኮኖሚን አቅምን  መሠረት ያደረገ የበጀት ቀመር ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ግልጽና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የ2018 በጀት ቀመር የማዘጋጀትና የማደራጀት ስራ ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈቃደስላስ ቤዛ ናቸዉ።

የዘንድሮውን የበጀት ቀመር የማዘጋጀቱ ስራ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት የተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ለበጀት ቀመር ዝግጅት መረጃዎችን የማናበብና የማጥራት ተግባር የተከናወነበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዚህም ስራ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ያሉ የሶስት ዓመት መረጃዎችን  የማመሳከር ስራ መሰራቱንም አክለዋል።

በመድረኩ የክልል፣የዞኖች እና የ3ቱ ሪጂዮፖሊስ ከተሞች ባለድርሻዎች ተገኝተውበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም