የአካባቢ መራቆት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለእንክብካቤ ሥራ ትኩረት ሰጥተናል - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢ መራቆት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለእንክብካቤ ሥራ ትኩረት ሰጥተናል

ወሊሶ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፡-የአካባቢ መራቆት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለእንክብካቤ ሥራ ትኩረት መስጠታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወንጪ ወረዳ የክልሉ መንግስት ሀላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ተጀምሯል።
በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉትና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች በአካባቢው መራቆት ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሀይሉ ጉልቲ በወንጪ ወረዳ የችግኝ ተከላ የተካሄደበት "ቱሉ ሶንቆሌ" ተራራ ከዓመታት በፊት በደን የተሸፈነ ነበር ብለዋል።
ተራራው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ተራቁቶ አፈሩም በጎርፍ እየተጠረገ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ ባለፉት የበጋ ወራት ተራራውን መልሶ ለማልማት የጠረጴዛ እርከን ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በተራራውና በአካባቢው የገጠመውን የመሬት መራቆት መልሶ እንዲያገግም የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን እየተከሉ መሆናቸውንና ለተተከሉ ችግኞች የሚያደርጉትን እንክብካቤ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
አቶ ሽፈራው ጎቡ በበኩላቸው የተራቆተ መሬት ተመልሶ አረንጓዴ እንዲለብስ ችግኝ መትከል ብቻ በቂ ባለመሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎችን ጭምር በማስተባበር ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
"ችግኝ መትከል ብቻውን በቂ ስላልሆነ የእንክብካቤ ሥራውም በቂ ትኩረትን ይሻል" ያሉት ደግሞ አቶ ወርቅነህ ታደሰ ናቸው።
"ችግኝ ተክሎ መሄድ ብቻ ሳይሆን እንዲጸድቅ እያንዳንዱ ሰው ሀላፊነቱን መወጣት አለበት፤ የተተከሉ ችግኞች ሁሉ ለፍሬ እንዲበቁ የበኩላችንን እንወጣለን'' ሲሉም አከልዋል።
አቶ ታደለ ድንቁ እና ወይዘሮ ወገኔ ድንቁም የሌሎቹን ሃሳብ የሚጋሩ ሲሆን በአካባቢያቸው የተተከሉ ችግኞች እንዲድቁም የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ችግኝ የሚተከለው ለዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ጭምር በመሆኑ የተተከለ ችግኝ ፍሬ እንዲያፈራ ሁሉም ሰው መንከባከብ አለበት ብለዋል።