ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር የብድር ክፍያ ሽግሽግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር የብድር ክፍያ ሽግሽግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦ የገንዘብ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) ጋር የብድር ክፍያ ሽግሽግ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
ስምምነቱ የቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የእዳ ሽግሽግ (G20 Common Framework debt treatment) አማካኝነት የተፈረመ ነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ስምምነቱን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ መግባቢያ ሰነዱ እ.አ.አ በማርች 2025 በመርህ ደረጃ የተደረሰውን የብድር ሽግሽግ (Debt treatment) በይፋ ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል።
ይህም ለኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን አመልክቷል።
ስምምነቱ ለአመታት ሲደረግ ለነበረው ድርድር ስኬታማ መቋጫ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የመንግስት እዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
ኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ አባላትን፣ በተለይም የኢትዮጵያን የዕዳ ሽግሽግ ጥረት በማገዝ ላሳዩት ጽኑ ድጋፍና ትብብር የኮሚቴው የጋራ ሰብሳቢዎች ለሆኑት ቻይና እና ፈረንሳይ ልባዊ ምስጋናዋን አቅርባለች።
የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ ስምምነቱ ከእያንዳንዱ የኮሚቴው አባላት ጋር በሚደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች አማካኝነት ተግባራዊ እንደሚሆን መግለጫው አመላክቷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት በእስከ አሁኑ ሂደት የተንጸባረቀው የትብብር መንፈስ በሁለትዮሽ ስምምነቶች ሂደት ወቅትም እንደሚቀጥል እንዲሁም ሂደቱን ለማፋጠን እንደሚረዳ የጸና እምነት አለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ አበዳሪዎች ጋር በትብብር መስራቷን ትቀጥላለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ከሀገሪቱ የዕዳ ሽግሽግ ፍላጎት እና ሁሉንም አበዳሪዎችን በተነጻጻሪ መንገድ ከማስተናገድ መርህ (Comparability of Treatment) ጋር በሚጣጣም መልኩ ስምምነቶችን ለመፈፀም እንደምትሰራ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከአበዳሪ ኮሚቴው ጋር የተደረሰውን መግባቢያ፣ የቦንድ ባለቤቶችን ጨምሮ ከሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት የበለጠ እንደሚያጠናክርም ነው ያመለከቱት።