የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተራቆተ መሬታችን እንዲያገግም አድርጓል

ሀዋሳ ፤ሰኔ 25/2017 (ኢዜአ) ፡-ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተራቆተ መሬታቸው እንዲያገግም ማድረጉን በሲዳማ ክልል የዳራ ኦቲልቾ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

የዳራ ኦቲልቾ ወረዳ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ልማት  የተራቆተ አካባቢና የተጎዳ መሬታቸው አገግሟል፡፡

ይህም በጎርፍ  የሚሸረሸረውን አፈር  ማስቀረትና ለከብቶቻቸው  የመኖ ሳር ማብቀል መጀመሩን ገልጸዋል፡፡


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አርሶ አደር ማርቆስ ኬንካ፤ ለጎርፍ የተጋለጠ መሬታቸው ላይ እርከን በመስራትና  በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን በመትከል  ለም አፈር በጎርፍ እንዳይጠረግ  ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህም የመሬቱን ለምነት በመጠበቁ ለከብቶቻቸው መኖ ማግኘታቸውንና  አካባቢያቸውን  ነፋሻ ማድረጉን  ተናግረዋል፡፡


 

ወይዘሮ አየለች ታደሰ በበኩላቸው የተጎዳ መሬታቸው በአረንጓዴ አሻራ ልማት እንዲያገግም በመደረጉ ጥምር ጥቅም የሚሰጡ  ችግኞችን  በመትከል  ተጠቃሚ መሆናቸውን  አንስተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተራቆተ  መሬትን  ስነ-ምህዳር በመቀየር  ምንጮችና ጅረቶችን ዳግም እንዲፈልቁ  ማድረጉን  የገለጹት ደግሞ ሌላኛው አርሶ አደር አክሊሉ ጥላሁን ናቸው፡፡


 

እሳቸውም የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በማስተባበር የእርከን ስራ ላይ የአፈር ለምነት እንዲጠብቅና የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ለተከታታይ ዓመት በሰሩት ስራ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው በክልሉ በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል፡፡


 

በዚህም የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ ለማልማት በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍ በመደረጉ የጽድቀት መጠኑ ማደጉንም ገልጸዋል፡፡

የሲዳማ ክልል አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በተገኙበት በዳራ ኦቲልቾ ወረዳ በይፋ መጀመሩ ይታወሰል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም