በመዲናዋ የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 95 በመቶው ወደ ቀጣይ ክፍል ተሸጋግረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 95 በመቶው ወደ ቀጣይ ክፍል ተሸጋግረዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በ2017 ዓ.ም የስድስተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከ75 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀጣዩ ክፍል መሸጋገራቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የፈተና ውጤቱን ይፋ መደረግ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል።
ኃላፊው በመግለጫቸው በትምህርት ዘመኑ 79 ሺህ 34 ተማሪዎች የስድስተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ መልቀቂያ ፈተናውን መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል 75 ሺህ 85 ወይም 95 በመቶ የሚሆኑት 50 እና ከዚያ በላይ አማካይ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ መሸጋገራቸውን አመላክተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተው፥ ይህም ለውጤቱ መገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ከዚህ በታች የተቀመጡ ማስፈንጠሪያዎችን በመጠቀም ከዛሬ ጀምሮ ውጤታቸውን ማየት እንደሚችሉ ተገልጿል።
ሊንክ https://aa6.ministry.et/#/result እና የቴሌግራም ቦት @emacs_ministry_result_qmt_bot