የህንድ የፈጠራ ማዕከል - ባንጋሎሩ - ኢዜአ አማርኛ
የህንድ የፈጠራ ማዕከል - ባንጋሎሩ

ቤተልሄም ባህሩ(ኢዜአ)
የዴልሂና አግራ ቆይታችንን ጨርሰን ወደ ቀጣይ መዳረሻችን ባንጋሎሩ ከተማ ልንጓዝ ስንሰናዳ አብዛኛው የጋዜጠኛ ልዑክ ያሳሰበው እንደሰም የምታቀልጠውን የአግራ ፀሀይና ሙቀት በባንጋሎሩም ታገኘን ይሆን? የሚለው ነበር። ሆኖም ከዴልሂ ኢንድራ ጋንዲ አየር ማረፊያ ተነስተን ለሶስት ሰዓት ከተቃረበ በረራ በኋላ ያገኘናት ባንጋሎሩ የተለየች ሆነን አገኘናት። ባንጋሎሩ ቀዝቀዝ ባለ አየር ነበር እንግዶቿን የተቀበለችን። በዕለቱ ከክፍሎቻችን ወጥተን በጋራ ወደአየር ማረፊያ የሚወስደንን ትራንስፖርት ስንጠባበቅ ከጋዜጠኛ ቡድኑ ስድስት አባላት ከአጠገባችን እንዳልነበሩ አስተዋልን። የት ጋር እንደተነጣጠልን አላስታውስም። በዚህ ምክንያት ግን የእለቱ ጉዟችን ተሰርዞ ከተማዋን ለማየት ስንዘዋወር የማውቀው ዓይነት እንጂ የተለየ ሙቀት አላስተናገድኩም።
የ13 ወር ፀጋ በመባል የምትታወቀው አገሬ ኢትዮጵያ ከዳሎል እስከ ራስ ዳሽን ባላት የመልከዓ ምድር አቀማመጥና ልዩ ልዩ የአየር ጠባይ ሙቀቱንም፣ ቅዝቃዜውንም ማወቃችን እንደዚህ ለአለ አጋጣሚ መልካም ስሜት ይፈጥራል። በተወሰነ ደረጃ በህንድ ያጋጠመኝ የአየር ባህሪ ከአገሬ ጋር ቢመሳሰልብኝ የፈጣሪንና የተፈጥሮን ስራ አጃኢብ ብዬ እንዳልፍ አድርጎኛል።
ባንጋሎሩ ከተማ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ማዕከል በመሆኗ የህንድ ሲልከን ቫሊ በመባል ትታወቃለች። ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ስፍራዎችም ከመገለጫዎቿ መካከል ናቸው።
የጠፈር ጠበብቶቹ - ባንጋሎሩ ደርሰን በመጀመሪያ ያየነው ዓለም በስፔስ ሳይንስ እየሰራች ያለችውና እያስመዘገበችው የምትገኘው ውጤት ማሳያ የሆነውን የህንድ ስፔስ ምርምር ድርጅትን ነው። ተቋሙ የህንድ መንግስት የስፔስ ዲፓርትመንት አካል ሲሆን፤ ዶክተር ቪክራም ሳራብሃይ በተሰኙ ባለራዕይ በ1962 የተወጠነና አሁን ላይ በዘርፉ ተገዳዳሪ መሆን የቻለ ነው። የተቋሙ ዓላማ የስፔስ ቴክኖሎጂዎችን በማልማትና በመተግበር ለተለያዩ አገራዊ ጥቅሞች ማዋል መሆኑን ተከትሎ የሳተላይት ማምጠቂያ መሳሪያዎችን የማምረት ስራን ጨምሮ ከአገሩ አልፎ ለሌሎች አገራትም በዘርፉ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። የተደረገልን ገለፃ አብዛኛውን ጋዜጠኛ ያስደመመ ነበር ከገለፃ በኋላ በጋዜጠኞች የተነሳው ሃሳብም ህንድ በስፔስ ዘርፍ ያላት ልምድና ያከናወነችው ተግባር በቀጣይም ልትሰራ የወጠነቻቸው ሃሳቦች የአገሪቱን መዳረሻ የተለሙ በአገራቸው እንዲተገበር የሚናፍቁት መሆኑን ነው። ተቋሙ በዘርፉ ለተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና በቀጣይም ትብብሩን የሚያጠናክር መሆኑን ከተደረገልን ገለፃ ተገንዝበናል።
በሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግና አስተዳደር ምሁራንን በማስተማር እያበረከተ ያለው የህንድ የሳይንስ ኢንስቲትዩት በባንጋሎሩ ከጎበኘናቸው መካከል የሚጠቀስ ነው። ኢንስቲትዩቱ ከአፍሪካ የተውጣጡ ተማሪዎችን የሚያስተምርና ከተቋማት ጋርም በዘርፉ የሚሰራ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ከጅማ፣ በተግባር ለመቀየር ሲታትሩ የስታርት አፖችን የምርት ውጤቶቻቸውን ሲፈትሹና ሲሞክሩ ተመልክቻለሁ። በኢትዮጵያም አሁን ላይ ለስታርት አፖች በተሰጠው ትኩረትና በተፈጠረው ምቹ ስነ ምህዳር የፈጠራ ውጤቶች እያደጉና እየተበራከቱ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። እንደ አዳማና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተቋማት የተማሪዎችን ፈጠራ ወደ ውጤት ለመቀየር እየተጉ መሆኑና የስታርት አፕ ኤግዚቢሽንና የሰመር ቡት ካምፖች ፈጠራን ምን ያህል እያበራከቱ መሆናቸው በጉብኝቱ ወቅት ወደ አዕምሮዬ የመጣ የአገሬው ህዝብ በውጤት የታጀበ ጥረት ነው።
ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በባዩቴክኖሎጂ ዘርፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የሚገኘው ባዮኮንም ከባላንጎሩ የጉብኝት መዳረሻችን መካከል የሆነና አስፈላጊ መድሀኒቶችን የሚያመርትና በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ላይም እየሰራ ያለ ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት የአቅም ግንባታ ስልጠናው ተጠቃሚ ናቸው። ከ120 በላይ በሆኑ አገራት ለስኳርና ካንሰር ህመም የሚያገለገሉ መድሀኒቶችን በማምረትና በማሰራጨት ለህሙማን ፈውስና ለጤናው ዘርፍ ስርዓት አስተዋፅኦ እያበረከተም ይገኛል። የተቋሙ ላቦራቶሪና ዘመኑን የዋጀና ደረጃውን የጠበቀ ማምረቻ ፋብሪካን መጎብኘቴ አለም በፋርማሲዩቲካልስ ዘርፍ ያለችበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው።
የባንጋሎሩ ቤተመንግስት - ይህን ቤተ መንግስት ማስቃኘቴን ከመጀመሬ በፊት በስፍራው ካስገረመኝ ነገር ላወጋችሁ ወደድኩ። ቤተ መንግስቱን ለመጎብኘት ያቀናነው በእለተ ሰኞ ነበር። ሆኖም ምድረ ግቢውን ቃኝተን ስለህንፃው ሰምተን ከመመለስ ውጪ ወደ ውስጥ አልዘለቅንም። ለምን? ለሚለው ምላሹ በዚህ ስፍራ "ሰኞ የእረፍት ቀን ናት" ነው። እንዴት ካላችሁ ቤተ መንግስቱ ቅዳሜና እሁድ በበርካታ ሰዎች የሚጎበኝ መሆኑን ተከትሎ በስፍራው ለሚሰሩ ሰራተኞች የእረፍት ቀናቸው ሰኞ በመሆኑ ነው። የቤተ መንግስቱ ምድረ ግቢ ሰፊና ልምላሜ የተላበሰ ሲሆን፤ የሚያምርና ለዓይን የሚስብ ኪነ ህንፃ ያለው ነው። አሰራሩና ውጥኑም እንደሚከተለው ነው። በዎዲየር ስርወ መንግስት ንጉስ ቻማራጃ ዋዲያር ወደ እንግሊዝ ባደረጉት ጉዞ በለንደን ዊንሶር ግንብ ይደነቃል። ተደንቆም አልቀረ የባንጋሎሩ ቤተ መንግስትን በተመሳሳይ ሁኔታ ይገነባል። ይህ ቤተ መንግስት በተወሰነ መልኩ የመካከለኛው ዘመን የኖርማንሲና የእንግሊዝ ግንቦችን ይመስላል።
ቪድሃና ሶውዳ የካራንታካ ህግ አውጪ አካል መናገሻ በጉብኝታችን ያየነው ሌላው መዳረሻ ስፍራችን ነው። የህግ አውጪና የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የያዘው ይህ ህንፃ ህንድ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ በራሷ መሀንዲስ የሰራችው የመጀመሪያው ህንፃ መሆኑ ተገልፆልናል። የህንፃ ግንባታ ጥበብ ማሳያ፣ የፖለቲካ መናገሻ እንዲሁም የባህል ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል።
እንደአጠቃላይ በቆይታዬ የተመለከትኩት የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ማበረታቻ እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ስራ ኢትዮጵያ እያከናወነች ካለው የኮሪደር ልማትና ስታርት አፕን የማበረታታት ብሎም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስነ ምህዳር ምቹነት ስራዎች ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ነው።
በህንድና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ፤ ለሁለት ሺህ ዓመታት የዘለቀ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያሳያል። የህንድና ኢትዮጵያ ግንኙነት በአክሱም ስርወ መንግስት ኢትዮጵያና ህንድ በአዱሊስ ወደብ በኩል የንግድ ልውውጥ ሲያደርጉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በወቅቱ ኢትዮጵያ ቅመማ ቅመምና ሐርን ከህንድ ትገበይ ነበር። ህንድ ደግሞ ወርቅና የዝሆን ጥርስን ከኢትዮጵያ ትሸምት ነበር። ህንድ ከንግድ ልውውጥ ባሻገር በኢትዮጵያ ኪነ ህንፃ ግንባታ ላይ አሻራዋን አኑራለች። በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍም ትልቅ አበርክቶ ያላት አገር ናት።
ህንድ ነፃነቷን ካገኘችበት እኤአ 1948 አንስቶ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት ኢትዮጵያና ህንድ ሌላው የሚያመሳስላቸው ነገር ሆኖ ያገኘሁት የአምራች ዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እያከናወኑ ያሉት ንቅናቄ ነው። ህንድ እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት "ሜድ ኢን ኢንዲያ" በሚል ለአስር ዓመት የተገበረችውና በርካታ ለውጥ የተመዘገበበት ንቅናቄ በኢትዮጵያ ከ2014ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ካለውና የሃገር በቀል ምርቶች እና አምራቾችን ማጠናከር፣ የኢንዱስትሪያል ማህበረሰብ ግንባታን ማሳደግ ፣ ምቹ የቢዝነስ ከባቢ መፍጠር እና የጥናት እና ምርምር ችግር ፈቺነትን ማሳደግን ዓላማ ካደረገው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጋር የተመሳሰለ ነው። ንቅናቄ በኢትዮጵያ መተግበሩ ዓመታዊ የዘርፍ ዕድገት፣ የማምረት አቅም አጠቃቀምና ገቢ ምርት በመተካት በኩል ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑም ይታወቃል።
በህንድ ተዘዋውሬ በተመለከትካቸው ከተማዎች ባሉ ጎዳናዎች ከታዘብኩት ነገር ሰዎች ከሱቅ ለሚገበያዩት ነገር ሳይቀር በዲጂታል መንገድ ክፍያ መፈፀማቸውን ነው። በባጃጅና በሞተር የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘትም ጭምር ሞባይሉን በመጠቀም “ይህ ቦታ የት ነው?” ሳይል ያሻዎት ስፍራ መድረስም ሌላው ትዝብቴ ነው። ይህ ነገር በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትኩረት አግኝተው እየተሰራባቸው ካሉት የዲጂታል ክፍያና ዲጂታል ክህሎት ማሳደጊያ መርሃ ግብር ጋር የሚመሳሰል ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
በቆይታችን ልክ እንደአትሌቶቻችን ሁሉ በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርጎ የሚያስነሳውን ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዝናና ክብር ለማስተዋል ችያለሁ። ፀጉረ ልውጥ መሆናችንን የተገነዘቡ በገበያ ማዕከላት የሚያገኙን እንዲሁም በምንጎበኛቸው ተቋማት የምንተዋወቃቸው ህንዳውያን "ከየት ናችሁ?" ብለው ሲጠይቁ፤ ለእኔና አንድ ከሌላ መገናኛ ብዙሃን የሄድን "ከኢትዮጵያዊ" ስንል የሚከተልልን ምላሽ "አሃ የኢትዮጵያ አየር መንገድ" የሚል ነው። ይህም አየር መንገዱ ስሙ ከኢትዮጵያ ተሰናስሎ የሚጠራ የአገሪቷ መታወቂያ ተቋም መሆኑን ያስገነዘበኝ ነው። ከህንዳውያን ጋር ብቻ ሳይሆን አብረን ከተጓዝን ጋዜጠኞች አንዱ "የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእናንተ የብቻ ሳይሆን እኛንም እንደራሳችን ሆኖ እያገለገለን ያለ የጋራ አየር መንገዳችን ነው" ሲል ነው የገለፀው። ይሄ ለእኔ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ኩራት ብቻ ሳይሆን መለያ ምልክትም ጭምር መሆኑን የተረዳሁበት አጋጣሚ ነው።
በቀናት ቆይታዬ በእንግዳ አክባሪነታቸውና በለገሱን ፍቅርና እንክብካቤ ከአገሬ የራቅኩ ያህል ሳይሰማኝ ብቸኝነትን ሳላስተናግድ እንደውም እየናፈኳቸው እንድመለስ ላደረጉኝ ህንዳውያን በከበረ ሰላምታ ላመሰግን እወዳለሁ።