በክልሉ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ቦንጋ ፤ ሰኔ 25/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወኑ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለፁ።

ክልል አቀፍ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃግብር በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱና ተጠቃሚነታቸውን በበለጠ የሚያረጋግጡ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡


 

የክረምት ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የማህበረሰቡን ኑሮ የሚቀይሩና ተጠቃሚነታቸውን በተጨባጭ የሚያረጋግጡ  ሥራዎች የሚከናወኑበት መሆኑን ጠቁመው ይኽው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል። 

''በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በልዩ ትኩረት እንደሚመራም አስታውቀዋል።

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ገነት መኩሪያ በበኩላቸው በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በ14 መስኮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል ።


 

የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳትና መልሶ ግንባታ፣ የአካባቢ ንጽህና ጥበቃ፣ ችግኝ ተከላ ፣ ደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም