ሰላምና ልማት ፀንቶ እንዲቀጥል የደሴ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ በሰልፍ የሰጠው ድጋፍ የሚበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምና ልማት ፀንቶ እንዲቀጥል የደሴ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ በሰልፍ የሰጠው ድጋፍ የሚበረታታ ነው

ደሴ ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፡- የደሴ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ የአካባቢው ሰላምና ልማት ፀንቶ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሰልፍ የሰጠው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ደህንነት መምሪያ አስታወቀ፡፡
ሰላምና ልማትን የሚደግፍ እንዲሁም ፅንፈኝነትን የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰልፍ ባለፈው እሁድ በደሴ ከተማ መከሄዱ ይታወቃል።
የሰልፉ ተሳታፊ ነዋሪ ሕዝብ በወቅቱ የመንግስትን የልማት እቅዶች በመደገፍና የሰላም ጥረቶች በማገዝ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
ከምንም በላይ ሰላምና ልማታችንን አጥብቀን እንሻለን ሲሉም ባስተላለፉት መልዕክት አረጋግጠዋል።
የደሴና አካባቢው ሰላም አስተማማኝ የሆነው በሕዝቡ ትብብርና በፀጥታ አካላት ትጋት መሆኑንና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም እንደሚደግፉም አመላክተዋል።
ነዋሪው ሕዝብ በሰልፉ ያስተላለፈውን መልዕክት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ሰላምና ደህንነት መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰይድ የሱፍ ፤ የከተማው ሕዝብ ባካሄደው ሰልፍ ልማትን በመደገፍና ፅንፈኝነትን በማውገዝ ሰላምን ለማፅናት ከመንግስት ጎን የተሰለፈ መሆኑን ማረጋገጡን ተናግረዋል።
በተለይ መንግስት አስተማማኝ ሰላም ያስፈን፣ ህግ ያስከብር፣ ያለ ስጋት ወጥተን እንግባ፣ ልማታችን ተጠናክሮ ይቀጠል፣ ልጆቻችን ይማሩ የሚሉ መልዕክቶችን ማስተላለፉ አመራሩ ይህንን በቁርጠኝነት ለማስፈፀም ይበልጥ ያነሳሳው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ሕብረተሰቡን በሚካሄዱ የሰላም ማስፈን ስራዎች በንቃት በማሳተፍ በሰላምና ልማት ላይ የበኩሉን እንዲወጣ የሚያበረታቱ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የከተማ አስተዳደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡