ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር ያስፈልጋል

ቦንጋ ፤ ሰኔ 25/2017 (ኢዜአ)፡- ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
"ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ" በሚል መሪ ሃሳብ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሚ በተገኙበት የፅዳት ዘመቻ በቦንጋ ከተማ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያው መረሃ ግብሩ ላይ ኢንጂነር ሌሊሴ ነሚ ባደረጉት ንግግር፤ የአካባቢን ንፁህና በመጠበቅ ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይገባናል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አባቶች ጠብቀው ያቆዩት ደን የአየር ብክለትን በማስወገድ ለኑሮ ተስማሚ ከባቢ እንዲፈጠር ምቹ መደላደል መሆኑን አንስተዋል።
ከተሜነት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የሚከሰትን ብክለት ለማስወገድ የቆሻሻ አወጋገድ ላይ ጥንቃቄን በማድረግ ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የአካባቢ ብክለትን ማስወገድና ፅዳትን ባህል ማድረግ ለጽዱ ኢትዮጵያ መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታን በመፍጠሩ ተግባሩን ባህል ማድረግ ይገባናል ያሉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ናቸው።
የፅዳት ዘመቻው አካባቢን ጽዱ ለማድረግ ፣ የቆሻሻ አወጋገድን ብቻ ሳይሆን ለአየር ብክለት ትኩረት በመስጠት ጤናን መጠበቅ የሚያስችል አቅምን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የፅዱ ኢትዮጵያን ንቅናቄ ከአረንጓዴ አሻራ ጋር በማስተሳሰር ለምግብነት የሚውል ችግኝ መትከልና የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ማጎልበትም እንዲሁ።
ከንቅናቄው ተሳታፊዎች መካከል የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፍርድነሽ ሀይሌ በሰጡት አስተያየት፤ የፅዳት ዘመቻው የአካባቢን ንፅህና ለመጠበቅ በጋራ የመስራትን ባህል ጎልብቶ እንዲቀጥል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
አመራሮቹ ከፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩ ሲሆን፤ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትንም አስጀምረዋል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።