ችግኝ በመትከል የምናደርገውን ተሳትፎ እናጠናክራለን -ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ችግኝ በመትከል የምናደርገውን ተሳትፎ እናጠናክራለን -ነዋሪዎች

መቱ፤ ሰኔ 25/2017 (ኢዜአ) ችግኝ መትከል የተጎዳ መሬት እንዲያገግምና ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑ ዘንድሮም በተከላው የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ የኢሉ አባቦር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
በኢሉባቦር ዞን የ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ማስጀመሪያ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዞኑ አሌ ወረዳ ተካሂዷል።
በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት አቶ ሲሳይ ወንድሙ፤ በየዓመቱ በተካሄዱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች እየተሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ችግኝ መትከል የተጎዳ መሬት እንዲያገግም የሚያግዝና ምርታማነትን የሚጨምር በመሆኑ እንደ ባለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም በተከላው በንቃት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ሌላው በችግኝ ተከላው የተሳተፉት አቶ ሁሴን ከበደ በግልና በጋራ በሚከናወኑ የችግኝ ተከላዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የአካባቢያቸው ገጽታ እየተለወጠ፣ ምርታማነትም እየተሻሻለ በመሆኑ ዘንድሮም ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
የአሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ከበደ በበኩላቸው በወረዳው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደ አቮካዶና ሙዝ ያሉ ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላላቸው ችግኞች ትኩረት ተሰጥቶ ተከላው እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ችግኝ መትከል ተተኪ ትውልድን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ የገለጹት ደግሞ የኢሉ አባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።
"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሐሳብ በሚከናወነው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞኑ ለተጎዱ መሬቶች ማገገምና ለኢኮኖሚያችን ማንሰራራት ጠቃሚ ለሆኑ ችግኞች ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።
በማስጀመሪያ መርሐግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻፊ ሁሴን፤ ችግኞችን መትከል የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅና የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው ምርታማ አካባቢን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በዚህ መርሐግብር የተከናወኑ ተግባራት ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ ብዙ የተጎዱ አካባቢዎች ዛሬ ላይ አገግመው ወደ አረንጓዴነት ተቀይረዋል ብለዋል።
በዚህም የተራቆተ መሬት ለምነቱ እየተመለሰና ምርታማነቱ እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፤ የደን ሽፋን መጠንም እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ሕብረተሰቡ አካባቢውን ሊቀይሩ የሚችሉና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።