የአዳማ ከተማን የኮንፍረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከልነት የሚያጎለብቱ ዲጂታል አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ ከተማን የኮንፍረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከልነት የሚያጎለብቱ ዲጂታል አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦የአዳማ ከተማን የኮንፍረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከልነት የሚያጎለብቱ የዲጂታል አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የከተማዋ ቱሪዝም ኮሚሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎችም ከተማ አስተዳደሩ አበረታች ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጓል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኮንፍረንስ ቱሪዝም በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዳማ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ ተስፋዬ ጎሳዬ አዳማ በኮንፍረንስ ቱሪዝም እያደጉ ከመጡ ከተሞች መካከል ተጠቃሽ መሆኗን ገልጸዋል።
የተለያዩ ስብሰባዎች እና ስልጠናዎች በአዳማ ከተማ እንደሚካሄዱ ጠቁመው፤ በከተማዋ ያሉ ሆቴሎችም ለስብሰባም ሆነ ለማረፊያነት የሚያገለግሉ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች እየሰጡ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ለዚህም ቱሪስቶች የሚያርፉባቸው 62 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መኖራቸውንና በአጠቃላይ 220 የሚጠጉ ሆቴሎች መኖራቸውን ገልጸው፤ በአንድ ጊዜ እስከ 32 ሺህ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም መኖሩን ተናግረዋል።
በአዳማ የሚገኙ ሆቴሎች የሚገኙበት ፖርታል መዘጋጀቱን እና ተጨማሪ የኦንላይን፣ ጎግል ማፒንግ እና የሞባይል አፕሊኬሽን ለማልማት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እነዚህ ወደ ስራ በሚገቡበት ወቅት የኮንፍረንስ ቱሪዝሙን ሙሉ እንደሚያደርጉት ተናግረዋል።
በተጨማሪም በርካታ ሆቴሎች እየተገነቡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለአብነትም ከ2012 እስከ 2016 ባሉት ጊዜያት 195 ፕሮጀክቶች በዚህ ዘርፍ ፈቃድ ወስደው እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በከተማዋ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ከቦታ ጀምሮ በርካታ ማበረታቻዎች እየተሰጡ መሆናቸውን እና አልሚዎች በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የስማርት አዳማ ፕሮግራም ለዘርፉ ዲጂታላይዜሽን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው፤ የሆቴሎች የሰው ሀይል አስተዳደር በሲስተም እንዲሆን ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ይህም ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በተናበበ መልኩ እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመው፤ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው ልማትም ዘርፉን በጉልህ እያሳደገው መሆኑንም ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች የስራ ሀላፊዎችም በከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ ተዋናዮች አበረታች ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል።
የኮንፍረንስ ቱሪዝምን የሚያጠናክሩ ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶች እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።