አዋጁ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በአግባቡ በመምራት የዜጎችን ክብርና ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው-ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
አዋጁ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በአግባቡ በመምራት የዜጎችን ክብርና ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው-ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚደረጉ የሥራ ስምሪቶችን በአግባቡ በመምራት የዜጎችን ክብርና ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 41ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
አዋጁ ዜጎች መብታቸው፣ ደህንነታቸው እና ክብራቸው እንዲጠበቅ የሚያደርግ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ብሔራዊ ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችል ነው።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ለኢዜአ እንደገለጹት፥ አዋጁ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪትን በተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌዎችን አካትቷል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መሆኑን ጠቅሰው፥ አዋጁም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አኳያ የዜጎች ደህንነትና የሀገር ጥቅም መነሻ እና መዳረሻ እንዲሆኑ ማድረግን የተመለከተ ነው ብለዋል።
አዋጁ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስቀረት ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው በመጥቀስ፥ በውጭ ሀገራት መስራት የሚፈልጉ ዜጎችም ክብራቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ በህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ያደርጋል ነው ያሉት።
በውጭ ሀገር ሥራ ላይ ሊሰማራ የሚችል ዜጋ የሥራ መደቡ የሚጠይቀውን የትምህርት ዝግጅት፣ ከፍተኛ የዘርፍ እውቀት፣ የሙያና የሥራ ልምድ እንዲኖራቸው የሚያስችል እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በሚቀጠሩበት የሥራ መስክ አግባብ ካለው የምዘና ማዕከል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ እንዲያገኙ የሚያደርግ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ጠንካራ የሆነ የስልጠናና የማብቃት ስርዓት አንዱ ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ዜጎች በራስ መተማመናቸውና የመደራደር አቅማቸው እንዲያድግ በማድረግ ረገድም አዋጁ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
አዋጁ የዘርፉ ተዋንያን ጠንካራ አደረጃጀትና የአሰራር ስርዓት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።