በድጋፍ ሰልፉ ሕዝቡ ያስተላለፈው መልዕክት አመራሩ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በቁርጠኝነት ይበልጥ እንዲተጋ መነሳሳትን የፈጠረ ነው

ጎንደር፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፡- በድጋፍ ሰልፉ ሕዝቡ  ያስተላለፈው መልዕክት እና የሰጠው እውቅና  አመራሩ ለዘላቂ ሰላም መፅናትና ልማት ቀጣይነት ከፊት ሆኖ በመምራት በቁርጠኝነት ይበልጥ  እንዲተጋ  መነሳሳትን  የፈጠረ ነው ሲሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ተናገሩ፡፡

በቅርቡ በአማራ ክልል የተለያዩ  አካባቢዎች ሰላምን የሚደግፍና ፅንፈኝነትን የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

ሕዝባዊ ሰልፉ ከተካሄደባቸው መካከል ጎንደር ከተማ አንዱ ሲሆን፤ የሰልፉ ተሳታፊ ነዋሪዎች በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤      ጎንደር በከፍተኛ የልማት ሥራ ላይ እንደምትገኝ በማመልከተ  ሰላሙንና ልማቱን ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኞች እንደሆኑ ተናግረዋል።

ከተማዋ ያገኘችው ዘርፈ ብዙ የልማት እድሎች ለህዝቡ የዘመናት የልማት ጥያቄ መሰረታዊ ምላሽ የሚሰጡ በመሆናቸው ለሰላም ዘብ በመቆም ልማቱን ለማስቀጠል የድርሻቸውን  ለማበርከት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ይህንን አስመልክቶ  ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ እንደገለጹት፤  ሕዝቡ የሰላሙም የልማቱም ባለቤት በመሆን ያበረከተው አስተዋጽኦ ለከተማው ሰላም መረጋገጥና ለልማቱ ስኬታማነት የጎላ ፋይዳ አለው፡፡


 

ጎንደር ታሪኳን ያደሰ አቧራዋንም ያራገፈ ውበቱዋንም የገለጠ የልማት፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑ በድጋፍ ሰልፉ ሕዝቡ ለመንግስት እውቅና የሰጠበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

''ሕዝቡ ሰላምና ልማትን አጥብቆ እንደሚሻና ይህን ለማደናቀፍ የሚሹ የጥፋት ተላላኪዎችን  እንደሚያወግዝ ጥብቅ መልዕከት አስተላልፏል'' ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤  አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕዝቡን ለማገልገል ዝግጁ እንዲሆን ያደረገም ነው ብለዋል፡፡

የከተማው ነዋሪ ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት በመኖሪያ አካባቢው እራሱን በማደራጀት ሰላሙን ለማረጋገጥ የወሰዳቸው እርምጃዎች ሰላም ፈላጊነቱንና ቁርጠኝነቱንም በድጋፍ ሰልፉ ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ህግን የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕዝቡ በድጋፍ ሰልፉ ያስተላለፈው መልዕክት ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ የፀጥታ መዋቅሩ ሕዝቡ የሰጠውን ተልዕኮና ሃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ያደረጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በፌዴራሉና በክልሉ መንግስት ድጋፍ በከተማው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለሕዝቡ ፍትሃዊ የመልማት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤  አመራሩ እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ እንዲበቁ ሌት ተቀን ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭና አመራር ሰጪነት በከተማው እየተካሄዱ የሚገኙት የኮሪደር ልማት ስራ፤ የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና እንዲሁም የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሕዝቡ አዎንታዊ ድጋፍ ከሰጣቸው የልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡  

ሕዝቡ ልማቱን አጥብቆ ከመደገፍ አንጻር የኮሪደር ልማት ስራው ስኬታማ እንዲሆን በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ ጭምር ላበረከተው አስተዋጽኦ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ እውቅና የሚሰጠው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በውጭና በሀገር ውስጥ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችና ባለሀብቶች ጭምር ከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በመሳተፍ ልማቱን በገንዘብ ለመደገፍ ያሳዩት ተሳትፎም ጎንደር ወደ ቀደመ ገናና ታሪኳና ስሟ እንድትመለስ በር የከፈተ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡

የድጋፍ ሰልፉ አመራሩ በጊዜ የለኝም መንፈስ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በላቀ ፍጥነትና ጥራት እንዲሁም ቁርጠኝነት በተግባር በማስመስከር ሀገርና ሕዝብን የማሻገር ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ታላቅ የቤት ስራ የሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባለፈው እሁድ ጎንደር ከተማን ጨምሮ በአማራ ክልል  የተለያዩ ከተሞች በተካሄዱት ሰልፎች ሕዝቡ ከያዛቸው መፈክሮች መካከል "ክልላችንን የሰላምና የልማት ማዕከል ለማድረግ  እንረባረባለን፤  ለሠላም ዘብ እንቆማለን፣ ፅንፈኝነትን እናወግዛለን፣ መንግስት ህግን በማስከበር የዜጎችን ሠላም ሊያስጠብቅ ይገባል የሚሉ ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም