ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀለ - ኢዜአ አማርኛ
ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀለ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ የመጨረሻ መርሃ ግብር ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሞንቴሬይን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ትናንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሜርሴዲስ- ቤንዝ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የጊኒው አጥቂ ሴርሁ ጉይራሲ በ14ኛው እና በ24ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥሯል።
ሜክሲኳዊው አጥቂ ጀርመን ቤርቴራሜ በ48ኛው ደቂቃ ሞንቴሬይን ከሽንፈት ያልታደገቸውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ተጨማሪ ግቦችን ሊያስቆጥርባቸው የሚችልባቸውን እድሎች አልተጠቀመም።
የጊኒው አጥቂ ሴርሁ ጉይራሲ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለ የመጨረሻው ቡድን ሆኗል።
በሩብ ፍጻሜው ከሪያል ማድሪድ ጋር ይገናኛል ። ማድሪድ ትናንት ማምሻውን ጁቬንቱስን 1 ለ 0 አሸንፏል።
የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብሮች የተጠናቀቁ ሲሆን የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሰኔ 27 እና 28 ቀን 2017 ዓ.ም ይደረጋሉ።
ፓልሜራስ ከቼልሲ፣ ፒኤስጂ ከባየር ሙኒክ፣ ፍሉሜኔንሴ ከአል ሂላል እና ሪያል ማድሪድ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ በሩብ ፍጻሜው የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።