ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስ በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፏል - ኢዜአ አማርኛ
ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስ በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፏል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2017 (ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ማለፍ ተጠባቂ መርሃ ግብር ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻዉን በሃርድ ሮክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የ21 ዓመቱ አጥቂ ጎንዛሎ ጋርሺያ በ54ኛው ደቂቃ ከትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ሎስ ብላንኮሶቹን አሸናፊ አድርጓል።
ተስፈኛው ወጣት አጥቂ ጋርሺያ በውድድሩ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል።
ሪያል ማድሪድ በጨዋታው የተሻለ ኳስ ቁጥጥር የነበረው ሲሆን ለግብ የቀረቡ እድሎችንም መፍጠር ችሏል።
ጉዳት ላይ የነበረው ኪሊያን ምባፔ ተቀይሮ በመግባት በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያ ተሳትፎውን አድርጓል።
ጁቬንቱስ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ወደ ሜዳ ይዞ የገባው የጨዋታ ስልት ውጤታማ አልነበረም።
ውጤቱን ተከትሎ ሪያል ማድሪድ የሩብ ፍጻሜ ትኬቱን ቆርጧል። ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና ሞንቴሬይ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
በጥሎ ማለፉ የመጨረሻ መርሃ ግብር ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከሞንቴሬይ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በሜርሴዲስ-ቤንዝ ስታዲየም ይጫወታሉ።