በክልሉ ከህዝብ ቁጥር ጋር የሚጣጣም የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፤ ሰኔ 24/2017(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ከህዝብ ቁጥር ጋር የሚጣጣም የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የክልሉን የሥነ-ህዝብ ምክር ቤት ጉባኤ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ አካሂዷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አራርሶ ገረመው(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በክልሉ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ከመምጣት ባለፈ ከፍተኛ የህዝብ ጥግግት አለ፡፡

በየጊዜው እያደገ ከሚመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር የሚጣጣም የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ለመቀጠል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ቢሮው ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከአገልግሎትና ሌሎች ዘርፎች ጋር ተባብሮ በመስራት እየተመዘገበ ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ከህዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር ለማጣጣም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የህዝብ ቁጥርን ወደ መልካም ዕድል በመቀየር በእውቀት የበቁ ዜጎችን ለማፍራት፣ ህዝቡ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለውን ቁርኝት ለማሳደግ፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና ለመሰል ሥራዎች ቢሮው ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የሴክተር ተቋማትን የአምስት ዓመታት አጠቃላይ ዕድገት ጠቋሚዎች ዝርዝር የያዘ የመረጃ ቋት መዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ ይህም ባለድርሻዎች በተደራጀ መረጃ ላይ የተመሰረተ ሥራ ለመስራት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዘማች ሂርጢባ የግብርናው ሴክተር ከክልሉ ጥቅል ምርት እድገት ከ43 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የሚመዘገበውን ዕድገት ለማስቀጠልና የህዝብን ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከፕላንና ልማት ቢሮ ጋር ተናበን እየሰራን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በክልሉ ያለውን የእርሻ መሬት መጠን የመለየት ሥራ መከናወኑን ጠቁመው ለእርሻ ሥራ በቂ መሬት የሌላቸውን በእንስሳት ልማትና በሌሎች ሥራዎች እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።፡

የሲዳማ ክልል ጤናና ጤና ነክ ግብዓት ጥራት ቁጥጥር አግልግሎት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ቡሪሶ ቡላሾ በዕቅድ የሚመራ ቤተሰብ እንዲኖርና የመኖር ምጣኔው ከፍ ያለ ማህበረሰብ ለመገንባት በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት የጤና መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት እንዲሁም ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ የማሟላት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም በክልሉ የመኖር ምጣኔን ከተቀመጠው የመኖር ምጣኔ ጋር ማጣጣም መቻሉን ጠቅሰው፣ የወሊድ ምጣኔንም ወደ 3 ነጥብ 91 ማውረድ ተችሏል ብልዋል።፡

በጉባኤው የሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የባህል ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም